AMN – ሰኔ 16/2018 ዓ.ም
የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ሊዲያ ግርማ፣ በከተማዋ ሕጋዊ የግብይት ሥርዓትን በማስፈን የተገኘው ውጤት ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉ ገልጸዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ የሕግ ማስከበርና ቁጥጥር ንዑስ ኮሚቴ ባለፉት ሰባት ወራት ያከናወናቸውን ተግባራት በመገምገም በቀጣይ ሦስት ወራት ዕቅድ ላይም ውይይት አድርጓል።
ኮሚቴው ጠንካራ ቅንጅታዊ አሠራሮችን በመከተል፣ በምርት ክምችትና ክዘና ላይ ከፍተኛ ቁጥጥር በማካሄድ ምርቶች ለሸማቾች በአግባቡ እንዲደርሱ የማድረግ ተግባራት ማከናወኑን ሰብሳቢዋ ገልጸዋል።

በቀጣይም ባልታደሰና ያለ ንግድ ፈቃድ የሚሰሩ፣ ከመስክ ውጪ የንግድ ሥራ ላይ የተሰማሩ እንዲሁም ከአድራሻ ውጭ የሚንቀሳቀሱ የንግድ ተቋማት ሕጋዊ ሥርዓትን በተከተለ የንግድ ሥርዓት ውስጥ እንዲገቡ የማድረግ ሥራዎች በቅንጅት እንደሚሠሩ አስታውቀዋል።
በከተማዋ ባሉ የገበያ ማዕከላት ላይ ከደላላ ነጻ የሆነ የምርት አቅርቦት እንዲኖር ቅንጅታዊ አሠራሩን ማጠናከር እንደሚገባም ወ/ሮ ሊዲያ አክለዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ደንብ ማስከበር ባለሥልጣን ዋና ሥራ አስኪያጅ ሻለቃ ዘሪሁን ተፈራ ፣ የተናበበ ቅንጅታዊ ሥራ በመሥራት ሸማቾች በቅዳሜና እሁድ ገበያ ላይ ጥራቱን የጠበቀ ምርት በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያገኙ ለማድረግ የተከናወኑ ተግባራት ውጤታማ እንደነበሩ ጠቅሰዋል።

ከተማ አስተዳደሩ ያስቀመጠውን አቅጣጫ መሠረት በማድረግ፣ በቀጣይ ሦስት ወራት የገበያ ማረጋጋት ላይ በትኩረት እንደሚሠራ ዋና ሥራ አስኪያጁ ገልጸዋል።
የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው በከተማዋ የሚስተዋሉ ሕገ-ወጥ የንግድ እንቅስቃሴዎች ላይ ጠንካራ ቁጥጥርና ክትትል በማድረግ፣ የተገኘውን ውጤት ይበልጥ ከፍ ለማድረግ እንደሚሠሩ ገልጸዋል።
በዳንኤል መላኩ