አዲስ አበባ “የብሪዝ ሲቲ” ከተሞችን ተቀላቀለች

AMN- ሰኔ 16/2018 ዓ.ም

አዲስ አበባ የብሪዝ ሲቲ ከተሞች አባል መሆኗ ዛሬ በለንደን የአየር ንብረት ለውጥ ትግበራ ሳምንት ፕሮግራም ላይ ተገልጿል።

አዲስ አበባ “የብሪዝ ሲቲ” ፕሮግራምን መቀላቀሏ በከተማዋ የአየር ጥራትን ለማሻሻል የሚደረገውን ስራ የበለጠ እንደሚድግፍ ተጠቅሷል።

“ብሉምበርግ” የተባለ ግብረ ሰናይ ድርጅት፣ የአየር ጥራትን ለማሻሻል 45 ሚሊዮን ዶላር በመመደብ በዓለም ላይ ከተመረጡ ከተሞች ጋር በቀጣይ ለመስራት አስታውቋል።

ፕሮግራሙ በብሉምበርግ ግብረ ሠና የድርጅት፣ “በክሊን ኤር ፈንድ” እና “በሲ40 ሲቲስ” አማካኝነት የሚደረግ ድጋፍ ሲሆን፣ አላማውም የከተሞችን የአየር ጥራት ለማሻሻልና ከአየር ጥራት ጋር ተያይዞ የሚመጣውን የጤና ጉዳት ለመቀነስ ያለመ ነው።

ይኽም አዲስ አበባን ጨምሮ በ16 ዓለማቀፍ ከተሞች የሚተገበር መሆኑን ነው የተገለፀው።

የፕሮግራሙ መገለፅን ተከትሎ የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በተወካያቸው “አዲስ አበባ የብሪዝ ሲቲ አባል መሆኗ ጠቀሜታ እንዳለው ገልጸው፣ በከተሞች የኮሪደር ስራ እያሳየን ያለውን ሁለንተናዊ የላቀ የከተማ ትራንስፎርሜሽን ፣ ፅዱ፣ ውብ፣ አረንጓዴ እና ለመኖር ምቹ ከባቢን ከመፍጠር ስራችን ጎን-ለጎን የአረንጓዴ አሻራ፣ የብስክሌት መንገድ እና የአየር ጥራት መቆጣጠርያ መሣርያዎችን የበለጠ አስፋፍተን እና አጠናክረን ለመስራት ያግዛል ብለዋል።

ጨምረውም “በማይክል ብሉንበርግ እንዲሁም በሚመሩት የግብረሰናይ ድርጅት እየተደረገልን ያለው እገዛም ይህንን አጠናክረን ለመስራት ያስችለናል ብለዋል።

እንዲሁም አዲስ አበባ የኮፕ 32ን ስታዘጋጀት በአየር ጥራት ቁጥጥር እና የአየር ጥራትን ማሻሻል የሚያስችሉ ተሞክሮዎችን ለሌሎችየአፍሪካ ከተሞች ብሎም ለአለም አቀፍ ከተሞች ተሞክሮ ለማሳየት ያግዘናል” ብለዋል ።

የተባበሩት መንግታት በአየር ንብረት ለውጥ ልዩ መልዕክተኛ እና የብሉምበርግ ግብረሰናይ ድርጅት ዋና መስራች ማይክል ብሉንበርግ በበኩላቸው፣ በብሪዝ ሲቲስ አማካኝነት የከተማ ከንቲባዎች እንዲሁም መሪዎች የአየር ጥራትን ከማሻሻል አንጻር ግንባር ቀደም ሆነው መስራታቸውን ቀጥለዋል ሲሉ ገልፀዋል።

እያንዳንዱ ከተማ ወደፊት አየር ጥራትን ከማሻሻል አንጻር የሚወስደው እርምጃ ሕይወትን ለማዳን፣ የሕዝብ ጤናን ለማሻሻል እና የብክለት ልቀትን ለመቀነስ ይረዳል – ይህም ከተሞች ለመኖርና ለመሥራት የተሻሉ ቦታዎችን ያደርጋል ብለዋል።

ይህ አዲስ ኢንቨስትመንት ወይም ድጋፍ ከንቲባዎች እያደረጉ ባለው ስራ ተጨማሪ እገዛ እንደሚያደርግና ከነዚህ ስራዎች የሚገኙ ተሞክሮዎችን ደግሞ ወደ ተጨማሪ ከተሞች ለማዳረስ እንደሚረዳ ገልፀዋል።

አሁን ከተቀላቀሉት አዲስ አበባ እና ማድሪድ ከተሞች በተጨማሪ፥ አክራ፣ ባንኮክ፣ ቦጎታ፣ ብራስልስ፣ ጃካርታ፣ ጆሃንስበርግ፣ ለንደን፣ ሜክሲኮ ሲቲ፣ ሚላን፣ ናይሮቢ፣ ፓሪስ፣ ሪዮ ዴ ጄኔሮ፣ ሶፊያ፣ እና ዋርሶ እንደሚገኙበት የአዲስ አበባ ከተማ ኮሙኒኬሽን ቢሮ መረጃ ያመላክታል።

ይህም ብክለትን ለመቀነስ እና የህዝብ ጤናን ለማሻሻል የሚሰሩ የከንቲባዎች አውታረ መረብ ይፈጥራል ተብሏል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review