የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር በአዲስ አበባ ሰፊ የስራ እድልና የኢኮኖሚ መነቃቃትን እየፈጠረ ነው

AMN- ሰኔ 17/2018 ዓ.ም

ኢትዮጵያ በተከታታይ የምታካሂደው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር የአየር ንብረት ለውጥን ሚዛን ከመጠበቅ ባሻገር፣ በአዲስ አበባ ከተማ ለበርካታ ዜጎች አዲስ የቢዝነስ እና የስራ እድል ምንጭ መሆን ችሏል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፣ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በተከናወኑ ግዙፍ የኮሪደር ልማቶች እና የታላላቅ ፓርኮች ግንባታ ሳቢያ የችግኝ ፍላጎት በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል።

በሚሊዮን የሚቆጠሩ የውበት፣ የጥላ እና የፍራፍሬ ችግኞችን ለልማት ፕሮጀክቶቹ ለማቅረብ በ11ዱም ክፍለ ከተማዎች በጥቃቅንና አነስተኛ የተደራጁ ማህበራት በችግኝ ማፍያ ጣቢያዎች ላይ ተሰማርተው ዓመቱን ሙሉ ቋሚና ጊዜያዊ ገቢ እያገኙ ይገኛሉ።

ከከተማዋ የሥራና ክህሎት ቢሮና ኢንደስትሪ ልማት ቢሮ የተገኘው መረጃ እንደሚያሳየው፣ ከአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር የእሴት ሰንሰለት ጋር ተያይዞ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች የስራ እድል ተጠቃሚ መሆን ችለዋል።

ከዚህ ውስጥ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ማዘጋጀት፣ የግብርና መገልገያ መሳሪያዎች ሽያጭ እና የችግኝ ማጓጓዝ የትራንስፖርት ስራዎች በከፍተኛ ሁኔታ ማደጋቸው በዘርፉ ሰፊ የንግድ እንቅስቃሴ መፈጠሩን ያሳያል።

የፍራፍሬ ችግኞች ላይ የተደረገው ትኩረትም በከተማ ዳርቻዎች የከተማ ግብርና እንዲስፋፋና ለምግብ ዋስትና የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያበረክት አድርጓል።

በከተማዋ ነባራዊ ሁኔታ በዚህ የአረንጓዴ ልማት ውስጥ ከ60 በመቶ በላይ የሚሆኑት ቀጥተኛ ተጠቃሚዎች በየክፍለ ከተማው በጥቃቅንና አነስተኛ ማህበራት የተደራጁ ሴቶች እና ወጣቶች መሆናቸውን መረጃዎች ያመለክታል።

በተለይም ከከተማዋ ደረቅ ቆሻሻ ተፈጥሯዊ ማዳበሪያ በማዘጋጀትና የፓርኮችን አረንጓዴ ቦታዎች በመንከባከብ ረገድ የሴቶች ማህበራት ተጠቃሚነታቸው ጎልቶ ታይቷል።

በሌላ በኩል፣ በክረምት ወቅት ጉድጓድ በመቆፈርና ችግኝ በመትከል፣ በበጋ ወቅት ደግሞ ውሃ በማጠጣትና በመንከባከብ ስራ ላይ የተሰማሩ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ቀጥተኛ የገቢ ምንጭ ያገኙ ሲሆን፣ ከዩኒቨርሲቲ በደን ሳይንስና ሆርቲካልቸር የተመረቁ ባለሙያ ወጣቶችም ሳይንሳዊ የቴክኒክ ድጋፍና ማማከር ስራዎችን በመስራት የቢዝነሱ ባለቤት መሆን ችለዋል።

እንደ የእንጦጦ፣ የወዳጅነት እና የአንድነት ፓርኮች ያሉ ታላላቅ አረንጓዴ ስፍራዎችን ተከትሎ በዙሪያቸው የተከፈቱ የካፌ፣ የፎቶግራፍ፣ የባህል አልባሳት ኪራይ መሰል የንግድ ቦታዎች ለበርካታ የከተማዋ ነዋሪዎች ቋሚ የኑሮ መደገፊያ እየሆኑ መጥተዋል፡፡

በአጠቃላይ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር የአካባቢ ጥበቃ ግብን ከማሳካት ባለፈ፣ ለአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች የኑሮና የስራ ዋስትና በመሆን የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ምሰሶነቱን በተግባር እያረጋገጠ እንደሚገኝ መረጃዎች ያመላክታሉ።

በአስማረ መኮንን

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review