በምስራቅ አፍሪካ ቀዳሚ የሆነውንና በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ቴክኖሎጂ የተደገፈውን እጅግ ዘመናዊ የላፍቶ ሆስፒታል መርቀን ለአገልግሎት ክፍት አድርገናል – ከንቲባ አዳነች አቤቤ

You are currently viewing በምስራቅ አፍሪካ ቀዳሚ የሆነውንና በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ቴክኖሎጂ የተደገፈውን እጅግ ዘመናዊ የላፍቶ ሆስፒታል መርቀን ለአገልግሎት ክፍት አድርገናል – ከንቲባ አዳነች አቤቤ

AMN ግንቦት 18/2018 ዓ.ም

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በምስራቅ አፍሪካ ቀዳሚ የሆነውንና በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ (AI) ቴክኖሎጂ የተደገፈውን እጅግ ዘመናዊ የላፍቶ ሆስፒታል፤ በዛሬው ዕለት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት መርቀን ለአገልግሎት ክፍት አድርገነዋል ብለዋል።

ከንቲባ አዳነች አቤቤ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት ለመላው የከተማችን ነዋሪዎች በሙሉ፤ እንኳን ደስ አላችሁ ያሉ ሲሆን ይህ ግዙፍ የህክምና ማዕከሉ በ5.4 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈ፣ 17 ዘመናዊ ህንፃዎችን ያቀፈ እና 500 አልጋዎችን የመያዝ አቅም ያለው ነው።

ሆስፒታሉ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ሆኖ የተገነባ ሲሆን ፤ በተለይም የካንሰር እና የልብ ህክምናዎችን በላቀ ደረጃ በመስጠት ዜጎች ለከፍተኛ ህክምና ወደ ውጭ ሀገር የሚያደርጉትን ጉዞ የሚያስቀርና የሀገርን የውጭ ምንዛሬ የሚያድን ነው ብለዋል።

ከዚህም ባሻገር፣ዘመኑ የደረሰባቸውን የላቁ የህክምና ቴክኖሎጂዎች ያካተተው ይህ ሆስፒታል፣ የሚከተሉትን ዘመናዊ አገልግሎቶችና ማሟያዎች በውስጡ ይዟል፦

• የላፍቶ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታልን በምሥራቅ አፍሪካ ብቸኛና ልዩ የሚያደርገው፣ በዓለም ላይ ያሉ የመጨረሻው የቴክኖሎጂ ውጤቶች የሆኑ፣ በሰው ሠራሽ አስተውሎት ወይም በ(Artificial Intelligence) የሚደገፉ እጅግ የረቀቁ መሣሪያዎችን ያሉት መሆኑ ነው።

ከእነዚህም መካከል፦

1. PET-SCAN (የቅድመና ድህረ ካንሰር ምርመራ ማሽን)፦ በምሥራቅ አፍሪካ የመጀመሪያው የሆነ፣ ሰው ሠራሽ አስተውሎት የተገጠመለትና የ2026 ምርት የሆነ የመጨረሻው ዲጂታል ቴክኖሎጂ የተሟላለትነዉ።

2. በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነና MRI- 3 Tesla “ የሂሊየም ትነትን ” ሙሉ በሙሉ የሚያስቀር (Zero Helium Boil-off) ድንቅ መሣሪያ፤

3. CT Scan፦ 640 Slice ልብ አንድ ጊዜ መትታ ሳትጨርስ (One-Beat Cardiac) ሙሉ ምርመራ ማድረግ የሚችል ፈጣን የምርመራ ቴክኖሎጂ፤

4• የልብና የደም ሥር ላቦራቶሪ (Cath Lab)፦ በቀጭን የደም ሥር በመግባት የልብና የአንጎል ደም ሥር ችግሮችን በአጭር ጊዜ ለይቶ የሚያክም የዘመኑ የመጨረሻ ጥበብ፤

5• Mammography (3D)፦ የጡት ካንሰርን በቅድሚያ ለመመርመርና በሁሉም አቅጣጫ የናሙና ምርመራ (Biopsy) ለመውሰድ የሚያስችል የረቀቀ መሣሪያ፤

6 • Robotic Laboratory (TLA)፦ ሙሉ በሙሉ ከሰው እጅ ንክኪ ነጻ የሆነ፣ የሰውን ስህተት በማስቀረት ፈጣንና ጥራቱን የጠበቀ ውጤት የሚሰጥ በሀገራችን የመጀመሪያው የላቦራቶሪ ሥርዓት የተሟሉለት ሲሆን፣

7 • ዘመኑ የደረሰበት የመጨረሻው የቴክኖሎጂ ውጤት የሆኑ የአልትራሳውንድ እና የዲጂታል ኤክስሬይ (X-Ray) ማሽኖችም ተሟልተውለታል።

8.በሰዓት 80 ሜትር ኩብ – ኦክስጂን የማምረት አቅም ያለውና የሜዲካል ጋዝ ማምረቻ ፕላንትንም ተሟልቶለታል፡፡

9. በብዙ ሆስፒታሎች የሚያጋጥሙት የኢንፌክሽን ችግርን ለማስቀረት የሆስፒታሉ ግድግዳዎችና ወለሎች ባክቴሪያን ሙሉ በሙሉ በሚከላከል (Anti-bacterial) ቁስ የተገነቡ ናቸው።

10 .ያልተቋረጠ ለዘላቂ አገልግሎት ለመስጠት ሲባል የራሱ የውኃ ጉድጓድ እና የፍሳሽ ማጣሪያ ፕላንት የተገጠመለት

11.ደረጃውን የጠበቀ 18 ዘመናዊ የአስከሬን ለረጅም ጊዜ ማቆየት የሚያስችል ማቀዝቀዣ እና ኡመሳሰሉት አካቷል።

በመጨረሻም፤ ለህብረተሰባችን የተሻለና ዘመናዊ ህክምናን ተደራሽ ለማድረግ የታለመው የዚህ ሆስፒታል ግንባታ በስኬት እንዲጠናቀቅ፣የደገፋችሁ ሌት ተቀን የለፋችሁ፣ እና ያስተባበራችሁ በየደረጃው የምትገኙ አመራሮች እንዲሁም መላው የአካባቢው ማህበረሰብ፤ በከተማ አስተዳደሩ እና በራሴ ስም ከልብ የመነጨ ምስጋናዬን አቀርባለሁ ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review