መንግስት ህብረ-ብሔራዊነትን በማጠናከር የሀገሪቱን ሰላምና እድገት ለማረጋገጥ እየሰራ ነው – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

You are currently viewing መንግስት ህብረ-ብሔራዊነትን በማጠናከር የሀገሪቱን ሰላምና እድገት ለማረጋገጥ እየሰራ ነው – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

AMN – ነሐሴ 2/2018 ዓ.ም

መንግሥት ሁሉንም ያካተተ ሕብረ-ብሔራዊነትን በማጠናከር የሀገሪቱን ሰላም እና ዕድገት ለማረጋገጥ በትኩረት እየሠረ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከኦሮሚያ ብሮድካስቲንግ ኔትዎርክ (OBN) ጋር ባደረጉት ቆይታ፣ በኦሮሚያ ክልልም ሆነ በሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች ለሚታዩ የጸጥታ ችግሮች የተለያዩ መነሻ ምክንያቶች እንዳሉ አብራርተዋል።

ለጸጥታ ችግሮቹ የመጀመሪያው ምክንያት ወደ ዴሞክራሲ ሽግግር በሚደረግበት ወቅት የሚያጋጥም ባህሪ ነው ብለዋል።

ታፍኖ የቆየን ፖለቲካዊ ምህዳር ዴሞክራሲያዊ ለማድረግ በሮች ሲከፈቱ፣ ሁሉም አካላት እኩል ኃይል እንዳላቸው ስለሚያምኑ እንደዚህ አይነት ክስተቶች ማጋጠማቸው በኢትዮጵያ ታሪክም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚታወቅ መሆኑን ጠቁመዋል።

አክለውም፣ ምንም እንኳን በሂደቱ መጀመሪያ ላይ እንደዚህ አይነት ባህሪያት ቢታዩም፣ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ወደ ንግግርና ተረጋግቶ ወደ መነጋገር መሸጋገሩ የማይቀር መሆኑን ገልጸዋል።

ይህ ሂደት ወደ ውይይት የሚያመራና ቀጣዩ እርምጃም በሕግ የበላይነት ማመን እንደሚሆን ነው ያስረዱት።

አሁንም ቢሆን የምክክር ሂደቶች እየተደረጉ እንደሚገኝና ውይይቶችን ተከተሎ የሚወጣው ሕግም ሁሉንም አካላት ተገዢ በሚያደርግ መልኩ የሚዘጋጅና ሁሉንም ያካተተ እንደሚሆን አብራርተዋል።

ሁለተኛው ምክንያት የስልጣን ማዕከል ለውጥ መሆኑን ያመለከቱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ሂደቱ ከትንሽ ቡድን ወደ ሁሉም አካል የሚሳተፍበት የስልጣን ሽግግር የሚደረግበት በመሆኑ እንደዚህ ዓይነት ሁኔታዎችን እንደሚፈጥር ገልጸዋል።

ይህም አንዱ የስልጣኑ ባለቤት ሆኖ ሌላው ደግሞ አጋር ብቻ ሆኖ የሚገፋበት አሰራር ማብቃት ስላለበት መሆኑን ተናግረዋል።

ሶስተኛው መሰረታዊ ምክንያት የማይታረቁ የጠላት ትርክቶች መሆናቸውን ጠቅሰው፤ ልዩነቶችን ዓለም አቀፍና የብሔር ብሔረሰቦችን ፍላጎት አለማክበር ችግሮችን ማስከተሉን ገልጸዋል።

የተያዘው መንገድ ግን ሁሉንም ተጠቃሚ የሚያደርግና ብሔር ብሔረሰቦችን አቅፎ የሚይዝ ህብረ-ብሔራዊነት መሆኑን አስምረውበታል።

አራተኛው ምክንያት ደግሞ የጠላቶች የረጅም ጊዜ ኢትዮጵያን የማፍረስ ፍላጎትና በአቋራጭ መንገድ ስልጣን ለመያዝ የሚደረግ ሙከራ እንደሆነ ገልጸዋል።

ይህም በተደራጀ መንገድ ሳይሆን መሳሪያ በመያዝና ሰዎችን በማጋደል ስልጣን ለመጨበጥ የሚደረግ ፍላጎት ሲሆን፣ የረጅም ጊዜ የኢትዮጵያ ጠላቶችም ይህንን አጋጣሚ እንደሚጠቀሙበት አብራርተዋል።

የሀገሪቱ ሰላም ባለፉት ዓመታት በብዙ ፈተናዎችና ችግሮች ውስጥ ማለፉን ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ህዝቡ ሁኔታውን መገንዘቡን አንስተዋል።

እንዲሁም ጠላቶች በግልጽ እየተዘጋጁና ትስስራቸውን እያጠናከሩ ቢሆንም ይህ ሁኔታ የሚሰበር መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህም አስተማማኝ ሰላምና የተረጋጋ ሁኔታ ተፈጥሮ ህዝቡ ወደ ስራው እንዲገባ ምቹ ሁኔታ ይፈጠራል የሚል ሙሉ እምነት እንዳላቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ አረጋግጠዋል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review