AMN – ነሐሴ 2/2018 ዓ.ም
መንግስት በሰላማዊ መንገድ ለመታገልና ለመወያየት ለሚፈልግ ማንኛውም አካል ሁልጊዜም በሩ ክፍት መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከኦሮሚያ ብሮድካስቲንግ ኔትዎርክ (OBN) ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ በሀገሪቱ ሰፊና አሳታፊ የዴሞክራሲ ምህዳር መፈጠሩን አንስተዋል።
ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ በርካታ ዜጎች ከእስር እንዲፈቱ መደረጉን ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ይሁን እንጂ አንዳንዶች ከእስር ከተፈቱ በኋላ ወደ ጫካ በመግባት ትናንት በደል ካደረሱባቸው አካላት ጋር በመጣመር ወደ ጥፋት ተልዕኮ መግባታቸውን ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅት ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሰላማዊ መንገድ ተንቀሳቅሰው የፖለቲካ ሀሳባቸውን በነፃነት ማቅረብና መግለጽ የሚያስችላቸው ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን ነው ጠቅላይ ሚንስትሩ የጠቆሙት።
በተለያዩ የፖለቲካ አመለካከቶች ላይ የተሰማሩ ተፎካካሪዎች በመንግስት ካቢኔ ውስጥ ጭምር እንዲካተቱ መደረጉ የፖለቲካ ምህዳሩን መስፋት እንደሚያሳይም አብራርተዋል።
የሁሉም ዜጋ ሀሳብ በእኩልነት የሚደመጥበትና ዘላቂ መፍትሔ የሚፈለግበት ሀገራዊ ምክክር እየተካሄደ መሆኑንም ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በማብራሪያቸው ጠቅሰዋል።