AMN – ነሐሴ 2/2018 ዓ.ም
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በኦሮሚያ ክልል ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ታጣቂ ኃይሎች የያዙት የትጥቅ ትግል በጫካ ውስጥ ተደብቀው ንፁሃንን ከመግደል እና ከመዝረፍ የዘለለ ምንም ዓይነት የፖለቲካ ግብ የሌላቸው መሆኑን ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከኦሮሚያ ብሮድካስቲንግ ኔትወርክ (ኦቢኤን) ጋር ባደረጉት ቆይታ፣ አሁን የትጥቅ ትግሉን ከሚመሩት አካላት ጀርባ ያለውን ተቃርኖ አንስተዋል።
አሁን ላይ በጫካ ውስጥ የሚገኙት ኃይሎች የማንን አጀንዳ እያስፈፀሙ እንደሆነ ሕዝቡና ወጣቱ ቆም ብሎ ሊጠይቅ እንደሚገባም ነው ያሳሰቡት።
መንግሥት ችግሮችን በሰላማዊ ውይይት ለመፍታት ያለው ቁርጠኝነት አሁንም ያልተለወጠ መሆኑን ያረጋገጡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ማንኛውም አካል በሰላማዊ መንገድ ሀሳቡን ይዞ ለመታገል እስከፈለገ ድረስ የመንግሥት የሰላም በር መቼም ቢሆን እንደማይዘጋ አስገንዝበዋል።
ጦርነት እና ግጭት አውዳሚ መሆናቸውን በመገንዘብ በየዕለቱ በሺዎች የሚቆጠሩ ታጣቂዎች የሰላምን መንገድ መርጠው ወደ ኅብረተሰቡ እየተቀላቀሉ እንደሚገኙም ተናግረዋል።
የኦሮሞን ሕዝብ ትግል በዋናነት የጀመሩ እና ያደራጁ አንጋፋ ፖለቲከኞች በአሁኑ ወቅት ሀገር ቤት ገብተው በፓርላማ እና በተለያዩ የንግድ ሥራዎች ላይ በሰላም እየተሳተፉ መሆናቸውን አብራርተዋል።
ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በጠመንጃ ኃይል ሊገነባ እንደማይችል ያመላከቱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ብልፅግና ፓርቲ በብቁ ሀሳብ እና በአሸናፊ ፖለቲካ ላይ የተመሠረተ እንጂ በዘር ላይ የተንጠለጠለ አደረጃጀት አለመሆኑን አብራርተዋል።
የትኛውም የፖለቲካ ቡድን ፍላጎቱን ማሳካት የሚችለው ሕዝብን አሳምኖ በምርጫ ሲያሸንፍ ብቻ መሆኑንም ገልጸዋል።