AMN ሰኔ 18/2018
ብልፅግና ፓርቲ ለህዝቡ የገባውን ቃል በተግባር በመፈጸምን ታሪካዊ ግዴታውን በብቃት እንደሚወጣ የፓርቲው ዋና ጽሕፈት ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ ሚኒስትርና የፌደራል ተቋማት አደረጃጀት አስተባባሪ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ፍቃዱ ተሰማ ገለጹ።
በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ዜጎች የመረጡት ሰላም፣ ዴሞክራሲ፣ ልማትና መልካም አስተዳደርን መሆኑንም ተናግረዋል።
የፌዴራል ተቋማት የብልፅግና ፓርቲ የፓርቲው አባል የፌዴራል ተቋማት ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት የሰባተኛው የጠቅላላ ምርጫ የማጠቃለያ ሪፖርት መድረክ በአዲስ አበባ እያካሄደ ነው።
አቶ ፍቃዱ ተሰማ በመድረኩ ባደረጉት ንግግር፤ የፌደራል ተቋማት አመራሮች ለሰባተኛው የኢትዮጵያ ጠቅላላ ምርጫው ስኬት አይተኬ ሚና መወጣታቸውን ገልጸዋል።
አመራሮቹ ምርጫውን በማስተባበር፣ በሱፐርቪዥን፣ በምርጫ ክርክሮች በንቃት በመሳተፍና ከሲቪል ማህበረሰብ ተቋማት ጋር ጠንካራ ግንኙነት በመፍጠር ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማበርከታቸውን ተናግረዋል።

ምርጫው ሰላማዊ፣ ፍትሐዊና ነፃ ሆኖ በብልፅግና ፓርቲ አሸናፊነት እንዲጠናቀቅ በማድረግም ታሪካዊ ኃላፊነትን መወጣት እንደተቻለ አብራርተዋል።
የምርጫው ስኬት ብልፅግና ፓርቲ ጠንካራ መዋቅር እንዳለው በተግባር የተረጋገጠበት ታሪካዊ ሁነት መሆኑን አንስተዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምርጫውን በስኬት በመምራት የኢትዮጵያን የዴሞክራሲ ተቋማት ጥንካሬ በተግባር ማሳየቱንም ገልጸዋል።
የፖለቲካ ፓርቲዎች በመልካም የፉክክርና ትብብር መንፈስ በመንቀሳቀስ፣ የሲቪክ ማህበራትና የመገናኛ ብዙኅን ሚዛናዊ ዘገባዎችን በማቅረብ ለምርጫው ስኬት ገንቢ ሚና መወጣታቸውን ጠቅሰዋል።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽንም ገለልተኛ ሆኖ ምርጫውን በመታዘብ ታሪካዊ ኃላፊነቱን መወጣቱን አብራርተዋል።

ህዝቡም በምርጫ ዕለት ከሌሊቱ አሥር ሰዓት በመነሳት እስከ እኩለ ሌሊት ድረስ በጽናት ድምፅ መስጠቱ ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ያለውን ቁርጠኝነት በተግባር እንዳረጋገጠ አስታውሰዋል።
በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ዜጎች የመረጡት ሰላም፣ ዴሞክራሲ፣ ልማትና መልካም አስተዳደርን እንደሆነም አስረድተዋል።
በዚህም ብልፅግና ፓርቲ በድህረ-ምርጫ ለህዝቡ የገባውን ቃል በተግባር በመፈጸም ታሪካዊ ግዴታውን በብቃት እንደሚወጣ አረጋግጠዋል።
የፌደራል ተቋማት አመራሮችም ፓርቲው የገባውን ቃል በብቃት በመፈጸም ለኢትዮጵያና ህዝቦቿ ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት በትጋት መስራት እንዳለበት አስገንዝበዋል።
See less