AMN- ሐምሌ 22/2018 ዓ.ም
1960ዎቹ መጨረሻ ላይ ሻዕቢያ ኤርትራን ከኢትዮጵያ ለመገንጠል በሚያደርገው ትግል፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ደርግን የሚያዳክምለትና የእርሱን የነጻነት ጥያቄ የሚደግፍለት የቅርብ ኃይል በትግራይ በኩል መኖሩ ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ ስላለው የእሱን እና የግብጽን ሀሳብ ተሸካሚ አድርጎ ማኅበር ገስገስቲ ብሔረ ትግራይ (ማገብት) ወደ ነፃነት ግንባር እንዲለወጥ በማድረግ ህወሓትን በአዲስ መልኩ አዋለደ፡፡
ዛሬም ድረስ ላይለያዩ የተቆራኙት ህወሓት እና ሻዕቢያም መርህ ላይ ያልተመሰረተ ግንኙነት ሲኖራቸው ፤ የጋራ ዓላማ ካላቸው አብረው የሚሰለፉ ፤ አንዱ የሌላውን ጥቅም ሲገፋ እርስ በእርስ የሚዋጉ በኢትዮጵያ አንድነት እና ነፃነት መንገድ ላይ የቆሙ ደንቃራዎች ናቸው፡፡
ህወሓት በትጥቅ ትግል ጊዜም ይሁን የማዕከላዊ መንግስቱን በመራበት ወቅት ከሀገሬው ህዝብ መርህ እና እሴት ያፈነገጠ ሀገር በቀል እሳቤን ያለተከተለ አፋኝ ስርዓትን በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ አንብሮ ነው የኖረው፡፡
ህወሓት የተከተላቸው በርካታ የውስጥ ቁጥጥር፣ የዲሲፕሊን ማስከበሪያ እና የተቃውሞ ማፈኛ ስልቶች ከአልባኒያው መሪ ኢንቨር ሆጃ እና ማርክሲስት-ሌኒኒስት የተኮረጁ ስለመሆናቸው በርካታ የታሪክ እና የፖለቲካ ልሂቃን በየመጽሐፎቻቸው የመሰከሩት ሀቅ ነው፡፡
እንደ የአልባኒያው ኢንቨር ሆጃ “ሲጉርሚ” የተባለ የስለላና አፈና መዋቅር ሁሉ ህወሓትም በደህንነት መዋቅሩ ውስጥ “የአጋዚ ኃይል” እና የ 1 ለ 5 አደረጃጀትን የኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ገቢራዊ አድርጎ ነው የቆየው፡፡
አልባኒያ 11ሺህ ስኩዌር ካሬ ሜትር የምትሸፍን በምስራቅ አውሮፓ የምትገኝ ትንሽ ሀገር ነች፡፡ ሀገሪቱ ከሁለተኛው የዓለም ጦርት ማብቃት ጀምሮ እ.አ.አ እስከ 1985 ድረስ ዓለምን ጉድ ያሰኘ ኢንቨር ሆጃ የሚባሉ አምባገነን መሪ አስተናግዳለች ፡፡ ሆጃ ለስልጣኑ ሲል የርዕዮተ ዓለም ልዩነት ያላቸውን የገዛ ሀገሩን ዜጎች ደፍጥጦና አዳፍኖ የመራ የአልባኒያ መሪ ነው፡፡
የኛው ሀገር ሕወሓት መራሹ መንግሥት ስልጣን ላይ በነበረበት ወቅት የሚከተለው ስርዓት የአልባኒያ የኮሚኒዝም ስርዓት መሆኑን በአደባባይ መናገሩ የማይካድ ሀቅ ነው፡፡
ሕወሓት የማዕከላዊ መንግስቱን በመራበት ወቅትም ከአልባኒያ የቀዳው የአፈና ተግባራት በኢትዮጵያዊያን ላይ ገቢራዊ ሲያደርግ ቆይቷል፡፡
ይህ ከአልባኒያ የተቀዳ የአፈና ተግባር ሕወሓት ዛሬም መገለጫዋ አድርጋ ቀጥላለች፤አሁን ላይም የህወሓት ታጣቂ ቡድን ያንን ያፈጃ ያረጀ የአፈና ዶሴ በመምዘዝ ዳግም በትግራይ ሕዝብ ላይ ለመተግበር አይኑን በጨው አጥቦ ብቅ ብሏል፡፡
አስገዳጅ የወታደራዊ ምልመላን ለማስፈጸም፤ በትግራይ ክልል በሕወሓት የተረቀቀው የአፈና ሕግ በሞት የሚያስቀጡ አንቀጾች በውስጡ ያቀፈ ሲሆን ፣ ህወሓት ዛሬም የትግራይን ሕዝብ ለቡድኑ ስልጣንና ህልውና ካልተዋጋና ካልሞተ፣ በሞት እቀጣለሁ የሚለውን መልዕክት በግልጽ ያስተላለፈ ነው፡፡
በስድስት ምዕራፎች የተከፋፈለው እና በ44 ገጽ የቀረበው የአፈና አዋጅ የአልባኒያው ኮሚኒዝም ኢንቨር ሆጃን የአፈና ስርዓት በትግራይ ህዝብ ላይ ዳግም ለመተግበር ያለመ ነው፡፡
አዋጁ ህወሓት የሚደግፉና የማይደግፉ በሚል የመደብ ልዩነት በመፍጠር እስከ የሞት ፍርድ የሚያደርስ ድንጋጌን ያያዘ ነው። ቡድኑ በ21ኛው ክፍለ ዘመን ላይ እንዲህ አይነት የአፈና ሕግ ማውጣቱ ድመት መንኩሳ አመሏን አትረሳ እንዲሉ የሕውሓት ጨቃኝ እና ረጋጭነት መቼም የማይለወጥ ባህሪው ለመሆኑ ማሳያ ነው፡፡
የሕወሓት ቡድን ፍላጎት የትግራይ ህዝብን መከራ በማብዛት የአንጃውን መሪዎች ጥቅም እና ስልጣን ማስቀጠል ሲሆን ፤ ህዝቡን በተደጋጋሚ ረብ በሌለው ጦርነት ውስጥ በማስገባት የትግራይ ህዝብን መከራ እያበዛ ይገኛል። የመሪዎቹ ምቾት እና ድሎት ግን አልተጓደለም። የትግራይ ወጣቶችን ከእናቶቻቸው ጉያ እየነጠቁ ወደ ጦርነት ሲማግዱ የእነሱ ልጆች እና ሚስቶቻቸው ግን በውጭ እና በአዲስ አበባ የተድላ ኑሮ እንዲኖሩ በማድረግ ነው፡፡
ህወሓት በአዲሱ አዋጁ አስገዳጅ የውትድርና ጥሪን ያስተላለፈ ሲሆን የትግራይን ወጣት የባዕዳን ቅጥረኛ በማድረግ ከዚህ ገቢ ለማግኘት እያደረገ ያለው ተግባር በትግራይ ሕዝብ ላይ የተፈፀመ ታሪክ ይቅር የማይለው ጥቁር ጠባሳ ነው፡፡
በአሳየናቸው ክፍሌ