AMN ሰኔ 19/2018
ኢትዮጵያ ያላትን ዓለም አቀፍ እና ቀጣናዊ ግንኙነቶች በመረጃ ላይ በተመሰረተ ትንተና በመምራት ብሔራዊ ጥቅሟን ማስከበር የሚያስችሉ ተግባራትን አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነት እና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዲማ ኖጎ (ዶ/ር) ገለፁ።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ መከላከያ ኮሌጅ አሁናዊ የኢትዮጵያ የብሔራዊ ደህንነት ተግዳሮቶችና የመፍትሄ አቅጣጫዎች በሚል መሪ ሃሳብ ዓመታዊ የደህንነት የምክክር ጉባዔ በትናንትናው እለት ተካሂዷል።
በጉባዔው ላይ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ወታደራዊ አማካሪ እና የተኩስ አመራር ኃላፊ ጀነራል አለምእሸት ደግፌ፣የመከላከያ የትምህርትና ስልጠና ዋና መምሪያ ሀላፊ ጀነራል ይመር መኮንን፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የምሥራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር ጌታቸው ረዳ፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ ቀነአ ያደታ (ዶ/ር)፣ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር ዘሪሁን አበበ ተገኝተዋል።
በዚህ ወቅት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነት እና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዲማ ኖጎ ( ዶ/ር ) እንዳሉት፤ በሀገር ውስጥ ያለ የትኛውም ችግር ሀገረ መንግስቱን መገዳደር የሚችል አይደለም፡፡

ስለሆነም ውጫዊ በሆኑ ተግዳሮቶች ላይ ማተኮርና ከአካባቢው ሀገራት ጋር ያለውን ግንኙነት አስቀድሞ በመተንተን መምራት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ያላትን ዓለም አቀፍ እና ቀጣናዊ ግንኙነቶች በመረጃ ላይ በተመሰረተ ትንተና በመምራት ብሔራዊ ጥቅሟን ማስከበር የሚያስችላትን ተግባራት አጠናክራ ልትቀጥል እንደሚገባም ገልፀዋል።
የኢትዮጵያ ባህር ኃይል ዋና አዛዥ ቫይስ አድሚራል ክንዱ ገዙ በበኩላቸው፤ ከጎረቤት ሀገራት ጋር በሚኖር ግንኙነት ገቢር ነበብ ስትራቴጂን መከተል እንደሚገባ አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ ባህር ኃይል ከተለያዩ ሀገራትና ዓለም አቀፍ የባህር ኃይል ተቋማት ጋር ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር የሚያስችሉ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑንም ተናግረዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ የምሥራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር ጌታቸው ረዳ፤ ኢትዮጵያ ሰላም እንዳትሆን የሚፈልጉ የሀገር ውስጥና የውጭ ኃይሎችን ለመመከት የውስጥ ጥንካሬን ማጎልበት ያስፈልጋል ብለዋል።
ኢትዮጵያ የአካባቢውን ሀገራትና ሕዝቦችን በልማት በማስተሳሰር ተጠቃሚነታቸውን እያረጋገጠች መሆኗ ተፈላጊነቷን ማሳደግ የሚያስችል መሆኑን ጠቅሰዋል።

ብሔራዊ ጥቅምን ባስከበረ አካሄድ ከጎረቤት ሀገራት ጋር የሚያስተሳስሩ መሠረተ ልማቶችን በማስፋፋት የተሻለ የጋራ ነገን መገንባት እንደሚገባ ተናግረዋል።
የኤርትራ ሀገረ መንግስት ህልውና ከኢትዮጵያ መዳከም ጋር የተያያዘ መሆኑን የገለጹት አቶ ጌታቸው፤ የሀገሪቱ መሪ ለስልጣኑ ማቆያነት በኢትዮጵያ ትርምስ መፍጠርን ቋሚ አጀንዳ አድርጎ ቢይዝም የማይሳካ መሆኑን ገልጸዋል።
የቀድሞ ህወሃት ጽንፈኛ ቡድንም ከስልጣን ውጪ መኖር የማይችል አመራር የያዘና የትግራይን ሕዝብ ሳይሆን የራሱን የስልጣን ጥም ለማርካት የሚተጋ መሆኑን አንስተዋል።
የትግራይን ሕዝብ የልማት ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ተስፋውን የሚያለመልሙ ተግባራትን ማጠናከር ይገባልም ማለታቸዉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡