AMN- ሰኔ 20/2018 ዓ.ም
የአስም በሽታ በሁሉም የዕድሜ ክልል የሚገኙ ሰዎችን የሚያጠቃ የረጅም ጊዜ የመተንፈሻ አካላት ሕመም ነው፡፡
በሽታው የአየር መተላለፊያ ቱቦዎች እንዲያብጡና እንዲጠቡ በማድረግ የመተንፈስ ሥርዓትን እንደሚያስተጓጉል በየካቲት 12 ሆስፒታል የውስጥ ደዌ ስፔሻሊስት ሐኪም የሆኑት ዶ/ር ሰላም ቦጋለ ከኤ ኤም ኤን ጋር በነበራቸው ቆይታ አብራርተዋል።
በሽታው በሚከሰትበት ጊዜም ትንፋሽ ማጠርና ለመተንፈስ መቸገር፣ የደረት መወጠር ወይም መጨናነቅ፣ በሚተነፍሱበት ጊዜ ከደረት የሚወጣ ድምፅ እንዲሁም በሌሊት ወይም በማለዳ የሚባባስ ሳል ዋና ዋናዎቹ ምልክቶች ናቸው።
የአስም በሽታን ከሚቀሰቅሱና ከሚያባብሱ ነገሮች መካከል፣ የአቧራ ብናኝ፣ የሶፋና የምንጣፍ ቆሻሻዎች፣ የቤት እንስሳት ፀጉር፣ የሲጋራና የማገዶ ጢስ፣ ጠንካራ የሽቶ ሽታዎች፣ ጉንፋን፣ የመኪና ጢስ፣ ጭጋጋማ አየር እና የአየር ሙቀት መለዋወጥ በዋናነት ይጠቀሳሉ።
በተለይም አሁን ካለው የክረምት ወቅት መግባት ጋር ተያይዞ የሚከሰተው ቅዝቃዜ፣ ጭጋጋማ አየርና የአየር ሁኔታ መለዋወጥ በሽታውን በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚቀሰቅሰው ዶ/ር ሰላም ገልጸዋል።

በክረምት ወቅት አየር በበቂ ሁኔታ ስለማይዘዋወር በቤት ውስጥ የሚፈጠሩ እርጥበቶች፣ የፈንገስ መራባትና የብናኝ ነፍሳት ለአስም ሕመምተኞች ተጨማሪ ሥጋት ይሆናሉ።
በተጨማሪም የክረምቱ ቅዝቃዜ የጉንፋንና መሰል የመተንፈሻ አካላት የቫይረስ ኢንፌክሽኖችን ስለሚያስፋፋ ይህም የአስም ስሜትን በእጅጉ ያባብሰዋል።
ይህንን ተጽዕኖ ለመከላከልና የአስም ስሜት በሚነሳበት ጊዜ የጠበቡ የመተንፈሻ ቱቦዎችን ለማዝናናት የሚረዱ ፈጣን እፎይታን የሚሰጡ እንደ “ሳልቡታሞል” ያሉ ማስታገሻ መድኃኒቶች መኖራቸውን ዶ/ር ሰላም አስረድተዋል።
የበሽታው ምልክቶች በሌሉበት ወቅት እንኳን እብጠትን ለመከላከል በሐኪም ትዕዛዝ በየቀኑ የሚወሰዱ እንደ “ኮርቲኮስቴሮይድ” ያሉ መድኃኒቶችን መውሰድ ስሜቱ ከመከሰቱ በፊት ለመከላከል እንደሚያስችልም ገልጸዋል።
የአስም በሽታ ተጠቂዎች በክረምት ወቅት ራሳቸውን ከበሽታው ለመከላከል የአልጋ ልብሶችን በሙቅ ውሃ ማጠብ እንዲሁም በቀዝቃዛ አየር ወቅት ወደ ውጭ በሚወጡበት ጊዜ አፍና አፍንጫቸውን መሸፈን እንዳለባቸው ባለሙያው ምክር ለግሰዋል።

ከመጠን በላይ የሆነ ክብደትን መቀነስና የተመጣጠነ ምግብ መመገብ በሽታውን ቀድሞ ለመከላከል አስፈላጊ ሲሆን፣ የሳንባ ኢንፌክሽንን ለመከላከልም በየዓመቱ የጉንፋን ክትባት መውሰድ ትልቅ እገዛ ያደርጋል።
የአስም ሕመም ምልክቶች በከፍተኛ ሁኔታ ከተባባሱ፣ የሚረጨውን መድኃኒት በመጠቀም በፍጥነት ማገገም ካልተቻለ እና ለመናገር እስከሚያስቸግር ድረስ የትንፋሽ ማጠር ከተከሰተ በአስቸኳይ ወደ ሕክምና ተቋም መሄድ እንደሚገባ ዶ/ር ሰላም አስገንዝበዋል።
አስምን ሙሉ በሙሉ ማዳን ባይቻልም እንኳን ሕመሙን ሊቀሰቅሱ ከሚችሉ ነገሮች መቆጠብና የሐኪምን ምክር መከተል እንደሚገባም ባለሙያው አስረድተዋል።
በበረከት ጌታቸው