AMN- ሰኔ 22/2018 ዓ.ም
በ7ኛው ዙር ሃገራዊ ምርጫ ያሸነፈችው ኢትዮጵያ ናት፤ ኢትዮጵያ እንድታሸንፍ ያደረጉት ህዝቦቿ ናቸው ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ባሰፈሩት መልዕክት፣ ውድ የከተማችን ነዋሪዎች ምርጫውን ዴሞክራሲያዊ፣ ፍትሃዊ፣ ነፃ ሆኖ በስኬትና በውጤት እንድናጠናቅቅ ስላደረጋችሁ እና የብልፅግና ፖሊሲና ስትራቴጂ ብሔራዊ ጥቅሞቻችን ያረጋግጣል ብላችሁ ፓርቲያችንን ብልፅግናን በአብላጫ ድምፅ ስለመረጣችሁ እናመሰግናለን ብለዋል።

ሃገርን ማፅናት፣ ሰላምን ዘላቂ ማድረግ፣ ብሔራዊ ጥቅማችንን ማረጋገጥ የኢትዮጵያችን የመቻል ማሳያዎች ናቸው ያሉት ከንቲባዋ፣ ለበርካታ የሚዲያ ዘመቻዎች፣ ከውጭም ከውስጥም ለነበሩ ጫናዎች ጆሮ ሳትሰጡ የኢትዮጵያን የመቻል አቅም ያረጋገጣችሁ የከተማችን ነዋሪዎችን በፓርቲያችንና በመንግስታችን ሥም እናመሰግናለን በማለት አክለዋል።
ሌሊት ወጥታችሁ ከቴክኖሎጂ መስተጓጎል ጋር በተፈጠረው እንግልት ሳትሰላቹ፣ ቀኑን ሙሉ ደከመኝ ሳትሉ እስከሌሊት በፅናት በመሰለፍ የኢትዮጵያ ዴሞክራሲ እንዲረጋገጥ አድርጋችኋል።

ልማታችን እንዲቀጥል፣ ሰላማችን እንዲረጋገጥ አድርጋችኋል፤ ፓርቲያችን ብልፅግናን ስትመርጡ ምንም ችግር የለም ብላችሁ ሳይሆን፣ ያልተመለሱ ጥያቄዎች በሂደት ይመለሳሉ፣ ያልጨረስናቸው ስራዎች በሂደት ያልቃሉ፣ የጎደለው ይሞላል ብላችሁ እምነት ሰጥታችሁ ነው ብለዋል።
የሰጣችሁን አደራ ነውና እኛም በታማኝነትና በመሰጠት፣ በትጋትና በቁርጠኝነት፣ 24/7 በመስራት አዲስ አበባን የብልፅግና ተምሳሌት ለማድረግ በቁርጠኝነት የምንሰራ መሆኑን ላረጋግጥላችሁ እፈልጋለሁ በማለት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።