AMN – ሰኔ 23/2018 ዓ.ም
ኢትዮጵያ በአንድ ጉብኝት ብቻ የተለያዩ የተፈጥሮ፣ የታሪክ እና የባህል ጸጋዎችን በጥምረት ማቅረብ የምትችል ብቸኛና ተመራጭ የቱሪስት መዳረሻ መሆኗን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሀገሪቱን የቱሪዝም ዘርፍ አስመልክተው በሰጡት ማብራሪያ ፣ የሀገርን ገጽታ ለመገንባት፣ የኢኮኖሚ ማገገሚያን ለማፋጠንና ብሔራዊ አንድነትን ለማጠናከር እየተከናወኑ ያሉ ተግባራትን ዘርዝረዋል።
በዚሁ ማብራሪያቸውም ቱሪዝም በብሔራዊ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ዕቅድ ውስጥ ካሉ አምስት ቁልፍ ዘርፎች አንዱ መሆኑን አስገንዝበዋል።
እንደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለጻ፣ ዓለም አቀፉ የቱሪዝም ዘርፍ የ12 ነጥብ 6 ትሪሊዮን ዶላር ሀብት የሚንቀሳቀስበት በመሆኑ፣ ኢትዮጵያ ከዚህ ዘርፍ የሚገባትን ድርሻ በማግኘት ሰፊ የሥራ ዕድል መፍጠርና አዳዲስ የውጭ ኢንቨስትመንቶችን መሳብ የምትችልበት ሰፊ ዕድል አላት።

ቀደም ሲል እንደ ኢትዮጵያ ያለችን ድንቅና ውብ ሀገር ስሟን በማጠልሸት በድህነት ብቻ እንድትታወቅና ውድቀቷን ብቻ አጉልተው በመናገር ሲሰሩ የቆዩ አካላት እንደነበሩ ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ይህን የተዛባ አመለካከት ለመቀየር መናገር ብቻ ሳይሆን ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ መጥቶ በተግባር እንዲያይ ማድረግ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የኢትዮጵያን የቱሪዝም መስህቦች “ከአፍሪካ ጥንታዊነት እስከ ምድራዊ ገነት” በሚል የገለጹት ዶ/ር ዐቢይ ፣ በአንድ በኩል የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ፣ የፋሲል ግንብ፣ የጎርጎራ ውበትና የጣና ጥንታውያን ገዳማት፤ በሌላ በኩል ደግሞ በአንድ አቅጣጫ ሁሉንም ዓይነት የአየር ንብረትና ብዝሃ ሕይወት አጣምሮ የያዘው የባሌ ተራሮች፣የሀረና ጥቅጥቅ ጫካ ፣ የብርቅዬው ጥቁር አንበሳ መገኛ እና የሶፍ ኡመር አስደናቂ የተፈጥሮ ዋሻ የኢትዮጵያ ልዩ መታወቂያዎች መሆናቸውን አብራርተዋል።
ኢትዮጵያ ከራስ ዳሽን ተራራ እጅግ ከፍተኛ ጫፍ እስከ ዳሎል ዝቅተኛ ቦታ ድረስ ባለው አስደናቂና ተቃራኒ መልክዓ ምድር፣ ከ6 ሺህ በላይ የዕፅዋት ዝርያዎችና በሌላው ዓለም የማይገኙ ብርቅዬ ሀገር በቀል እንስሳት ባለቤት መሆኗም ጠቅሰዋል።
ይህም ሀገሪቱ በአንድ ጉዞ ብቻ ተፈጥሮን፣ ታሪክን፣ ቅዝቃዜንና ሙቀትን በአንድ ላይ አጣምራ ማቅረብ የምትችል በዓለም ላይ ብቸኛ ሀገር ያደርጋታል ብለዋል።
በበረከት ጌታቸው