AMN- ሰኔ 24/2018 ዓ.ም

በ2010 ዓ.ም የነበረውን አገራዊ ለውጥ ተከትሎ የኢትዮጵያ የነገ ጉዞ ፍኖተ-ካርታ ሆኖ የተወለደውና በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የተጻፈው የ«መደመር» መጽሐፍ፣ ኦፊሴላዊ የቻይንኛ ቋንቋ የትርጉም ሥራው በመጠናቀቅ ላይ ይገኛል።
በቅርቡም ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ ለንባብ ሊበቃ መሆኑ ተረጋግጧል።
ባለፉት አሥርት ዓመታት ከአፍሪካ አህጉር ፈልቀው ወደ ዓለም መድረክ ከተሻገሩ ጥቂት አገር በቀል ፍልስፍናዎች መካከል ግንባር ቀደሙ የሆነው «መደመር»፣ አሁን ላይ ተደራሽነቱ እየሰፋና በርካቶች በትኩረት የሚመለከቱት አጀንዳ እየሆነ መጥቷል።
ቻይና የትርጉም ሥራውን እያጠናቀቀች ባለችበት በዚህ ወቅት፣ መጽሐፉ ከዚህ ቀደም በአማርኛ፣ በአፋን ኦሮሞ እና በእንግሊዝኛ ቋንቋዎች ካለው ተደራሽነት በተጨማሪ፣ በቅርቡ በአረብኛ እና በፓኪስታኑ የኡርዱ ቋንቋዎች ተተርጉሞ በደማቅ ሁኔታ መመረቁ ይታወሳል።
አሁን ደግሞ በቢሊዮኖች የሚነገርለትን የቻይናን መድረክ በይፋ ለመቀላቀል በመጨረሻው ምዕራፍ ላይ ይገኛል።
የ«መደመር» መጽሐፍ ወደ ቻይንኛ ቋንቋ መተርጎምና አሁን ላይ ኃያል ከሆኑ አገራት መካከል የምትጠቀሰውን ቻይናን ትኩረት መሳቡ፣ ከመጽሐፍ ትርጉም ሥራ ባለፈ በርካታ ስትራቴጂካዊና ፖለቲካዊ አንድምታዎችን ይዟል።
እንደ ቻይና ዓይነት እጅግ የዳበረ የረጅም ዘመን የፖለቲካ ፍልስፍና ታሪክ ያላት፣ እንዲሁም ከማኦ ዜዱንግ እስከ ዴንግ ዚያኦፒንግ፣ አሁን ደግሞ እስከ ፕሬዝዳንት ሺ ጂንፒንግ የዘለቀ የራሷ የርዕዮተ-ዓለም መስመር ያላት አገር «መደመር»ን ኦፊሴላዊ በሆነ መንገድ ወደ ራሷ ቋንቋ መተርጎሟ፤ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መድረክ ላይ ተፅዕኖ ፈጣሪና ትኩረት ሳቢ ፍልስፍና ማበርከት መቻሏን ማረጋገጫ ነው።
ይህም ኢትዮጵያ ባለፉት ዘመናት ከውጭ የሚመጡ ርዕዮተ-ዓለሞችን (ካፒታሊዝም/ሶሻሊዝም) ስታስተናግድ የኖረችበትን የታሪክ ምዕራፍ በመቀየር፣ አሁን ግን የራሷን አገር በቀል ፍልስፍና ወደ ውጭ የምትልክ አገር ለመሆኗ የ«መደመር» መጽሐፍ ትልቅ ማሳያ ነው።
መጽሐፉ አፍሪካን፣ መካከለኛው ምስራቅን (በአረብኛ)፣ ደቡብ እስያን (በኡርዱ) እና አሁን ደግሞ ምስራቅ እስያን (በቻይንኛ) ተደራሽ ማድረጉ፣ ፍልስፍናው ከተወለደበት የኢትዮጵያ ምድር ተሻግሮ አህጉራትንና የተለያዩ ባህሎችን የማስተሳሰርና የማቀራረብ ትልቅ የዲፕሎማሲ አቅም እንዳለውም ከብልፅግና ፓርቲ የተገኘው መረጃ ያሳያል።