AMN-ሰኔ 24/2018 ዓ.ም

32 ሀገራት እየተሳተፉበት የሚገኘው የጥሎማለፍ ዙር የዓለም ዋንጫ ጨዋታዎች ዛሬም ይቀጥላሉ። እንግሊዝ ከ ዲ.ሪ ኮንጎ ፤ ቤልጂየም ከ ሴኔጋል እንዲሁም አሜሪካ ከ ቦስኒያ ሄርዞጎቪና በጉጉት የሚጠበቁ ጨዋታዎች ናቸው።
እንግሊዝ ከ ዲ.ሪ ኮንጎ
በምድብ ጨዋታዎቿ በርካቶችን ያሳመነ ብቃት ያላሳየችው እንግሊዝ ከዲ.ሪ ኮንጎ ፈታኝ ጨዋታ ይጠብቃታል። በቶማስ ቱኸል የሚመሩት ሶስቱ አናብስት ሰባት ነጥብ በመሰብሰብ ምድብ 12ትን በቀዳሚነት ቢያጠናቅቁም ከጋና ጋር አቻ ፣ ፓናማን ደግሞ 2ለ0 ባሸነፉበት ጨዋታ ያሳዩት ብቃት ደጋፊዎቹን አላስደሰተም።
በጨዋታዎቹ እንደ ቡድን ከወሰዱት የበላይነት ይልቅ ሀሪ ኬን እና ጁድ ቤሊንግሃም በግላቸው ያሳዩት ብቃት ጎልቶ ወጥቷል። የባርን ሙኒኩ አጥቂ ሀሪ ኬን በተካፈለባቸው የዓለም ዋንጫ ውድድሮች ያስቆጠራቸውን ግቦች 11 አድርሷል። ይህም የሀገሪቱ የምንጊዜም ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ አድርጎታል።
እንግሊዝ ምንም እንኳን አሳማኝ ብቃት አታሳይ እንጂ ጀርመናዊው አሰልጣኝ ቶማስ ቱኸል ብሔራዊ ቡድኑን ከተረከበ በኋላ በ11 የፉክክር ጨዋታዎች በአንዱም አልተሸነፈችም። 10 ጨዋታዎችን ስታሸንፍ በአንዱ ብቻ ነጥብ ተጋርታለች።
ከ52 ዓመታት በኋላ ወደ ዓለም ዋንጫው የተመለሰችው ዲ.ሪ ኮንጎ በምድብ 11 ከፖርቹጋል ጋር አቻ ተለያይታ ፣ በኮሎምቢያ ተረትታ ፣ ኡዝቤኪስታንን ደግሞ አሸንፋ አራት ነጥብ በመያዝ ነው ሦስተኛ ሆና ያለፈችው።
አፍሪካዊቷ ሀገር በዓለም ዋንጫ የጥሎ ማለፍ ጨዋታ ላይ ስትሳተፍ የዛሬው ለመጀመሪያ ጊዜ ነው። ጠንካራ የመከላከል አቅም ያላት ኮንጎ በዛሬው ጨዋታ ይህን ጥንካሬዋን ለማጉላት ወደ ሜዳ ትገባለች ተብሎ ይጠበቃል። በውድድሩ ሦስት ግቦችን ያስመዘገበው የኒውካስትሉ አጥቂ ዮአን ዊሳ የሚገኙ ጥቂት ዕድሎችን ወደ ግብነት ለመቀየር የተዘጋጀ ተጫዋች ነው።
በጨዋታው በእንግሊዝ በኩል ዴክለን ራይስ ወደ መጀመሪያ አሰላለፍ ውስጥ ይገባል ተብሎ ይጠበቃል። ተጫዋቹ ፓናማን ባሸነፉበት የምድብ የመጨረሻ ጨዋታ ላይ በመጠነኛ ጉዳት ምክንያት አልተሳተፈም ነበር።
እንግሊዝ እና ዲ.ሪ ኮንጎ ከዚህ ቀደም በየትኛውም ውድድር ተገናኝተው አያውቁም። የመጀመሪያ ግንኙነታቸው የሆነው የዛሬ ጨዋታ በአትላንታ ስታዲየም ምሽት 1፡00 ላይ ይጀምራል።
ቤልጂየም ከ ሴኔጋል
በመጀመሪያዎቹ ሁለት ጨዋታዎቿ በፈረንሳይ እና ኖርዌይ የተሸነፈችው ሴኔጋል ለጥሎ ማለፍ ዙር አልተጠበቀችም ነበር። በመጨረሻ የምድብ ጨዋታዋ ኢራቅን 5ለ0 ማሸነፏ በውድድሩ እንድትቆይ አግዟታል።
ቤልጂየምም ቢሆን በምድብ ጨዋታዎቿ አሳማኝ ብቃት አላሳየችም። ከግብፅ እና ኢራን ጋር ነጥብ የተጋራችው ቤልጂየም ኒውዝላንድን 5ለ1 ማሸነፏ ምድቡን ቀዳሚ እንድትሆን ረድቷታል።
በታሪካቸው ለመጀመሪያ ጊዜ የሚገናኙት ቤልጂየም እና ሴኔጋል በሲአትል ስታዲየም የሚያደርጉትን ጨዋታ ምሽት 5፡00 ላይ የሚጀምሩ ይሆናል።
አሜሪካ ከ ቦስኒያ ሄርዞ ጎቪና
የ2026ቱ ዓለም ዋንጫ የጣምራ አዘጋጇ አሜሪካ በመጨረሻ የምድብ ጨዋታዋ በቱርኪዬ ከመሸነፏ ውጪ በርካቶችን ያስደመመ ብቃት አሳይታለች።
በመጀመሪያ ሁለት የምድብ ጨዋታዎቿ ፓራጓይ እና አውስትራሊያን ያሸነፈችበት መንገድ በውድድሩ ለማንም ፈታኝ መሆን እንደምትችል ያሳየችበት ነበር።
በማውሪሲ ፖቼቲኖ የምትመራው አሜሪካ መጠነኛ ጉዳት ገጥሞት የነበረው ክሪስቲያን ፑሉሲክን መልሳ ታገኛለች።
ቦስኒያ በዓለም ዋንጫው የጥሎ ማለፍ ጨዋታዎች ላይ ስትሳተፍ በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።
በዓለም ዋንጫ ውድድር ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚገናኙት አሜሪካ እና ቦስኒያ በሳንፍራንሲስኮ ቤይ ኤሪያ ስታዲየም ለሊት 9:00 ሲል ጨዋታቸውን ይጀምራሉ።
በሸዋንግዛው ግርማ