የጫኖ- ጨንቻ መንገድ ፕሮጀክት የደረሰበትን ፈጣን የግንባታ ሂደት ዛሬ ተመልክተናል – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

You are currently viewing የጫኖ- ጨንቻ መንገድ ፕሮጀክት የደረሰበትን ፈጣን የግንባታ ሂደት ዛሬ ተመልክተናል – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

AMN-ሰኔ 26/2018 ዓ.ም

የጫኖ-ጨንቻ መንገድ ፕሮጀክት የደረሰበትን ፈጣን የግንባታ ሂደት መመልከታቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ገለጹ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማሕበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት ፣ የ22 ኪሎ ሜትር የጫኖ-ጨንቻ መንገድ እና የ7 ኪሎ ሜትር የኤዞ-ጊርጫ ቅርንጫፍ መንገድን የያዘው የ29 ኪሎ ሜትር ፕሮጀክት በጥሩ አፈጻጸም ላይ ሲሆን፣ 13.3 ኪሎ ሜትር ስራው ተጠናቋል ብለዋል።

የመንገዱ ስራ ‎ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅ የማኅበረሰቡን ትስስር ይበልጥ ያጠናክራል፣ ንግድ እና ጉዞን ያቀላጥፋል፣ እንዲሁም የአካባቢውን የኢኮኖሚ ልማት ያፋጥናል ሲሉም ገልጸዋል።

‎በዚሁ ጉብኝታችን፣ ከ1997 ዓ.ም ጀምሮ በማህበረሰቡ ጠንካራ መሪነት የያዘውና የታደሰውን የዶርዜ ሎጅ የቱሪዝም መዳረሻ ጎብኝተናል ሲሉም አክለዋል።

በ40 ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ፣ በቀዝቃዛውና ሰንሰለታማ የተራራ ጋራ ላይ ያረፈው ይህ አስደናቂ ሥፍራ፣ የአባያና ጫሞ ሐይቆችን እንዲሁም “የእግዜር ድልድይ” ተብሎ የሚጠራውን የተፈጥሮ ድንቅ ዕይታ በአንድ ላይ በግልጽ የሚያሳይ ውብ ገጽታን ይሰጣል ሲሉም አክለዋል።

‎እንደ ዶርዜ ሎጅ ያሉ መሰል የቱሪስት መዳረሻዎች ጎን ለጎን የሚከናወነው የመንገድ መሠረተ-ልማት መስፋፋት፣ ስፍራው ያለውን እጅግ ከፍተኛ የኢኮኖሚና የባህል አቅም ሙሉ በሙሉ አውጥቶ ለመጠቀም በእጅጉ እንደሚያግዝም ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የገለጹት።

በመሆኑም፣ በሃገር ውስጥ እና በውጭ ሃገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና የዲያስፖራ አባላት፣ እንዲሁም ከመላው ዓለም የሚመጡ ጎብኚዎች ይህንን አስደናቂ የተፈጥሮ ውበትና የበለጸገ የባህል ሐብት እንዲጎበኙና የታሪኩ ተጋሪ እንዲሆኑ ጥሪዬን አቀርባለሁ ብለዋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review