AMN-ሰኔ 27/2018 ዓ.ም

የ23ኛው ዓለም ዋንጫ አድማቂ የሆነችው ኬፕ ቨርድ በአርጀንቲና ተሸንፋ ከውድድሩ ውጪ ሆናለች።
በሚያሚ ስታዲየም በተደረገ ጨዋታ ኬፕ ቨርድ ሌላ ዓለምን ያስገረመ ፍልሚያ አሳይታለች።
የሦስት ጊዜ የዓለም ዋንጫ አሸናፊዋ አርጀንቲና ሊዮኔል ሜሲ 29ኛው ደቂቃ ላይ ባስቆጠረው ግብ ብትመራም ጨዋታው አልቀለላትም።

ሜሲ በዘንድሮ ውድድር ያስቆጠራቸውን ግቦች ወደ ሰባት ከፍ አድርጓል። በአጠቃላይ የዓለም ዋንጫ ግቦቹን 20 አድርሷል።
ኬፕ ቨርድ ዴሮይ ዱአርቴ ባስቆጠረው ግብ አቻ ሆናለች። መደበኛው 90 ደቂቃም 1ለ1 ተጠናቋል።
በጭማሪ 30 ደቂቃ ሊሳንድሮ ማርቲኔዝ አርጀንቲናን ወደ መሪነት የመለሰች ግብ አስቆጥሯል።

እጅ መስጠትን ያልመረጡት ኬፕ ቨርዴዎች ሲድኒ ሎፔስ ካብራል ከመረብ ባሳረፈው አስደናቂ ኳስ በድጋሚ አቻ ሆናለች።

በኬፕ ቨርዴው ተጫዋች ዲኒ ቦርጌስ በራስ ላይ የተቆጠረው ግብ ግን አርጀንቲናን ለሦስተኛ ጊዜ መሪ አድርጓል። ጨዋታውም በአርጀንቲና 3ለ2 አሸናፊነት ተጠናቋል።

አፍሪካዊቷ ሀገር ኬፕ ቨርድ በመጀመሪያ የዓለም ዋንጫዋ ታሪክ መቼም የማይዘነጋው ፍልሚያ አሳይታ በክብር ወደ ሀገሯ ተሸኝታለች።
አርጀንቲና ደግሞ በ16ቱ ጥሎ ማለፍ ሌላኛዋን የአፍሪካ ተወካይ ግብፅን ትገጥማለች።
በሸዋንግዛው ግርማ