AMN- ሰኔ 27/2018 ዓ.ም

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን “ብቁ የበይነ መረብ መገናኛ ብዙሃን ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም” በሚል መሪ ቃል የውይይት መድረክ እያካሔደ ይገኛል።

የበይነ መረብ መገናኛ ብዙሃን (ዲጂታል ሚዲያዎች) ነጻነታቸውን ከኃላፊነት ጋር በማጣመር፣ ሀገርን ከሐሰተኛ መረጃና ከጥላቻ ንግግር ጥቃት ሊታደጉ እንደሚገባ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ሃይማኖት ዘለቀ አስገንዝበዋል።
ባለሥልጣኑ በበይነ መረብ መገናኛ ብዙሃን አገልግሎት ወቅታዊ ሁኔታና በየወራቱ በተደረጉ የሚዲያ ይዘት ክትትል ሪፖርቶች ላይ ከዘርፉ አመራሮችና ባለሙያዎች ጋር የውይይትና የስልጠና መድረክ እያካሄደ ይገኛል።

በመድረኩ ላይ እንደተገለጸው፣ መንግሥት ባደረገው የሚዲያ ዘርፍ ሪፎርም በሀገሪቱ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የበይነ መረብ መገናኛ ብዙሃን በሕግ ዕውቅና እንዲያገኙ ተደርጓል።

በዚህም መሠረት በአሁኑ ወቅት 73 ያህሉ ሕጋዊ የምዝገባ ምስክር ወረቀት አግኝተው በሥራ ላይ እንደሚገኙ ዳይሬክተሯ ገልጸዋል።
ዲጂታል ሚዲያዎች በቴክኖሎጂ አማራጮች አማካኝነት በሁሉም ቦታ በቀላሉ ተደራሽ መሆናቸውና የሐሳብ ብዙኃንነትን ማረጋገጣቸው በተጠቃሚው ዘንድ ተመራጭ እንዳደረጋቸው አንስተዋል።

ተቋማቱ በሕዝቦች አብሮነት፣ በሀገር ሉዓላዊነት፣ በታላቁ ህዳሴ ግድብ፣ በባህር በርና በዲፕሎማሲ እንዲሁም በሀገር ገጽታ ግንባታ ላይ ለሚያበረክቱት አዎንታዊ ሚናም ምስጋና አቅርበዋል።
ይሁን እንጂ፣ ዲጂታል ሚዲያውን ለአሉታዊ ዓላማ በመጠቀም በሕዝብና በሀገር ደህንነት ላይ አደጋ የሚደቅኑ፣ የጥላቻ ንግግርና ሐሰተኛ መረጃ የሚያሰራጩ አካላት መኖራቸው በይዘት ክትትል መረጋገጡን ወ/ሮ ሃይማኖት ገልጸዋል።
ይህ ነጻነትን ከኃላፊነት ባለማጣጣም የሀገርን ህልውና እስከ መፈታተን የደረሰ ጎጂ ልምምድ በዕንጭጩ ሊታረም እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
በመሆኑም የበይነ መረብ መገናኛ ብዙኃን የሀገሪቱን ሕጎች፣ የጋዜጠኝነት ሙያ ሥነ-ምግባርን እንዲሁም የሕዝብን እሴትና ባህል አክብረው እንዲሠሩ አቅጣጫ መቀመጡን ተናግረዋል።
ዘርፉን ከሐሰተኛ መረጃ ለመከላከልም ለአመራሮችና ለባለሙያዎች በሐቅ ማጣራት (Fact-Checking) ዙሪያ ቴክኒካዊ ሥልጠና የሚኸሰጥ መሆኑን ገልጸዋል።
በተጨማሪም የሚዲያ ተቋማቱ የራሳቸውን የሙያ ማህበር በማቋቋም እርስ በርስ የሚተራረሙበትንና የስነ-ምግባር ደንብ የሚያወጡበትን አሰራር እንዲዘረጉ ጥሪ አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣንም ለዘርፉ ሁለንተናዊ ዕድገት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።
በታምራት ቢሻውና ሄኖክ ዘነበ