AMN ሰኔ 27/2018

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የውስጥ ባንዳና የውጭ ታሪካዊ ጠላቶችን ከንቱ ህልም በማምከን የሀገርን ሉዓላዊነት በአስተማማኝነት እየጠበቀ መሆኑን የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ገለጹ።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ መከላከያ ኮሌጅ በመከላከያና ስትራቴጂክ የደህንነት ጥናት መስክ ሲያሰለጥናቸው የቆየውን ተመራቂዎች አስመርቋል።

በመርሃ ግብሩ ላይ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላምና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዲማ ኖጎ (ዶ/ር)፣ የኮሌጁ አዛዥ ብርጋዴር ጀነራል ጥላሁን ደምሴ እና ከፍተኛ ጄኔራል መኮንኖች ተገኝተዋል።

ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በሥነ-ስርዓቱ ባስተላለፉት፤ ወቅታዊ ዓለም አቀፋዊና ቀጣናዊ የደህንነት ሁኔታ ውስብስብና ኢ-ተገማችነትን ታሳቢ ያደረገ ሥራ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያን የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄና ቀጣናዊ የትብብር መርህ ለማደናቀፍ የታሪካዊ ጠላቶችና የውስጥ ባንዳዎች የሴራ ጥምረት ወይም “ፅምዶ” ፈጥረው እየሰሩ መሆኑን ጠቁመዋል።

ጀግናው የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊትም የውስጥ ባንዳና የውጭ ታሪካዊ ጠላቶችን ከንቱ ህልም በማምከን የሀገርን ሉዓላዊ ሰላምና ደህንነት በመጠበቅ ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ለዘመናት በሰላም እጦት የሚገለፀው የቀይ ባሕርና አፍሪካ ቀንድ አከባቢ የደህንነት ሁኔታ ከምንጊዜውም በላይ እየተወሳሰበ መምጣቱን አንስተዋል።
ኢትዮጵያ በቀጣናው የምትገኝ፣ ከማንኛውም የቀጣናው ችግርና ተጠቃሚነት ማምለጥ የማትችል ትልቅ ሀገር መሆኗንም አስገንዝበዋል።
ታሪካዊ ጠላቶችም ኢትዮጵያ ቀጣናውን የማረጋጋት የመሪነት ሚና እንዳትወጣና በውስጥ ጉዳዮች ብቻ እንድትጠመድ ለማድረግ ጥረት እያደረጉ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በሌላ በኩልም ጎረቤቶችን እንዲታመሱ በማድረግ ለውስጣዊ ደህንነታችን ጫና መፍጠር የሚችሉ ሴራዎችን በመሸረብ ቀጣናውን ለማተራመስ አበክረው እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።
ታሪካዊ ጠላቶች ኢትዮጵያን ከባሕር ዳርቻ ለማስወጣት የተጠቀሙበት የረጅም ዘመናት ሴራም ዛሬ ላይ ፅምዶ በሚል ስያሜ ዕድሳት ተደርጐለት እየተስተጋባ ነው ብለዋል።
የዘመኑ ጦርነት በሰው ሰራሽ አስተውሎት፣ በረጅም ርቀት ሚሳኤሎች፣ በሰው አልባ መሣሪያዎችና በሳይበር ኦፕሬሽኖች የታገዘ የቴክኖሎጂ ጦርነት መሆኑን አስረድተዋል።
በዚህም የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊትም አደረጃጀቱንና ዘመናዊ ትጥቁን በማጠናከር በማንኛውም አስተማማኝ የዝግጁነት ደረጃ ቁመና ላይ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ መከላከያ ኮሌጅ ተመራቂዎችም የቀሰሙትን ስትራቴጂክ ዕውቀት ለሠራዊቱ ተጨማሪ ግንባታ ሊጠቀሙበት እንደሚገባ አሳስበዋል።
የኮሌጁ አዛዥ ብርጋዴር ጄኔራል ጥላሁን ደምሴ በበኩላቸው፤ በሀገራዊ ለውጡ ማግስት የተመሰረተው ኮሌጁ በተለዋዋጭ ስትራቴጂክ ምህዳር ውስጥ የብሔራዊ ኃይል ማስፈፀሚያ አቅሞችን ውጤታማ ለማድረግ እየሰራ ነው ብለዋል።
ኮሌጁ የስርዓተ ትምህርት ማሻሻያ በማድረግ በጥናት፣ ምርምርና የደህንነት ትንተና ላይ ትኩረት አድርጎ የአመራር አቅም ግንባታ ስራዎችን እያከናወነ መሆኑንም አብራርተዋል።
መንግሥት የኮሌጁን የመሰረተ ልማትና የዲጂታላይዜሽን አቅም በማሳደግ ወደ ስማርት ኮሌጅ ለመቀየር የሚያደርገውን ጥረት አጠናክሮ እንደሚቀጥል መግለጻቸዉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡