አርባ ምንጭ ተመራጭ የቱሪዝም መናኸሪያ እንድትሆን የከተማዋ ወጣቶችና ነዋሪዎች የድርሻቸውን ሊወጡ ይገባል – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

AMN- ሰኔ 27/2018 ዓ.ም

የአርባ ምንጭ ከተማ ነዋሪዎችና ወጣቶች ወደ አካባቢው የሚመጡ ቱሪስቶች ተመላልሰው እንዲጎበኙና ከተማዋ የቱሪዝም መናኸሪያነቷ እንዲቀጥል የድርሻቸውን እንዲወጡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጥሪ አቀረቡ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በከተማዋ የተከናወኑ የቱሪስት መዳረሻ ስፍራዎች የምረቃ ሥነ-ሥርዓት ላይ ባደረጉት ንግግር፣ የአርባ ምንጭ ሕዝብ ለቱሪስቶች ሊያደርገው ስለሚገባ እንክብካቤና መልካም ስነ-ምግባር ዙሪያ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ለጉብኝት ወደ አካባቢዉ የሚመጡ ቱሪስቶች በአካባቢዉ የተፈጥሮ ጸጋዎች ተደስተዉ ለቀናት በአርባ ምንጭ እንዲቆዩ የአካባቢዉ ማህበረሰብ እንግዶችን ሊቀበልና በመልካም ሥነ ምግባር ሊያስተናግዳቸዉ ይገባል ብለዋል፡፡

በቱሪስቶች ላይ የሚፈጸሙ አልባሌ ድርጊቶች ከተገኙም በነዚህ ጥቂት ግለሰቦች ምክንያት የአካባቢዉም ሆነ የሃገር መልካም ገጽታ እንዳይጠለሽ እንደ ፖሊስና የፀጥታ አስከባሪ ሆነዉ ለቱሪስቶች ደህንነት የድርሻዉን ሊወጣ እንደሚገባ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አሳስበዋል።

አርባ ምንጭና አካባቢው በፍቅርና በሰላም የሚታወቅ፣ በሌሊትም ጭምር በነፃነት የሚንቀሳቀሱበት አስተማማኝ ቀጠና መሆኑን የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ቱሪስቶች መጥተው የሚተኙ ሳይሆን ተንቀሳቅሰው ገንዘባቸውን እንዲያወጡ የሰላም ጉዳይ ከምንም በላይ ጥንቃቄ ሊደረግበት ይገባል፡፡

“ባለቤት ያለው ከተማ ወይም ቤት አይቆሽሽም” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ነዋሪው ለከተማዋ የፅዳት እሴት ትኩረት በመስጠት አካባቢውን በንፅህና እንዲጠብቅም ጠቅላይ ሚኒስትሩ መልዕክት አስተላልፈዋል።

የአርባ ምንጭ ወጣቶችና ነዋሪዎች ቱሪስቶችን በፍቅርና በደስታ በመቀበል፣ ንብረታቸውንና ሰላማቸውን በማስጠበቅ በምድርም በሰማይም የከበረ ማንነት እንዲኖራቸውና ከተማዋን የቱሪዝም ተመራጭ እንዲያደርጓት አደራ ተጥሎባቸዋል ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው።

በአስማረ መኮንን

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review