AMN – ሐምሌ 8/2018 ዓ.ም
የምስራቅ አፍሪካ በይነ መንግስታት ድርጅት(ኢጋድ) ዋና ፀሐፊ ወርቅነህ ገበየሁ(ዶ/ር) የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ጉባዔ በሀገሪቱ ታሪክ ውስጥ አዲስ ምዕራፍ የሚከፍት ወሳኝ የታሪክ እጥፋት መሆኑን ገልፀዋል።
ዋና ፀሐፊው የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ጉባዔ ማስጀመሪያ መድረክ ላይ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር ፤ ሰላማዊ ውይይት ለሀገር ግንባታ ያለውን ፋይዳ ያብራሩ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ የገጠሟትን ችግሮች ለመፍታት ወደ ውስጧ መመልከት እንዳለባትም በአፅንዖት አሳስበዋል።
ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ በሀገራት ታሪክ ውስጥ ግጭት መፍትሄ አምጥቶ እንደማያውቅ ገልፀው ፣ ዘላቂ ልማትና ዕድገት ሊመጣ የሚችለው በሰላማዊ መንገድ ብቻ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

ዛሬ በብዙ መልኩ የበለጸጉና የተሻሉ የሚባሉ ሀገራት ፣ ከምንም ነገር በላይ የጋራ ሀገራቸውን ስላስቀደሙ ፣ ስለተደማመጡና በጠረጴዛ ዙሪያ ስለተነጋገሩ ብቻ ነው ሀገራቸውን ወደ ላቀ ደረጃ ማድረስ የቻሉት ብለዋል።
ኢትዮጵያ የራሷ የሆኑና ለዘመናት የቆዩ በርካታ የማስታረቂያ ፣ የይቅርታና የችግር መፍቻ ባህላዊ እሴቶችና ስርዓቶች ያሏት ሀገር መሆኗንም ገልፀዋል፡፡
ለአብነትም የሀገር ሽማግሌዎችን ጥበብ ጨምሮ እስከ ጥንታዊ ባህላዊ ህጎች ድረስ ኢትዮጵያ የራሷን ቁስል የምታክምበት ቁልፍ በእጇ ላይ ያለ ሀገር ናት ብለዋል።
በበረከት ጌታቸው