AMN- ሐምሌ 8/2018 ዓ.ም

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና የኮፕ 32 ፕሬዚዳንት ጌዲዎን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) ከኮፕ 21 ፕሬዚዳንት ሎረን ፋቢየስ ጋር ተወያይተዋል።
በውይይቱም ጌዲዎን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር)፤ የፓሪሱ ስምምነት ለዓለም አቀፍ የአየር ንብረት እርምጃዎች ያለውን ዘላቂ ጠቀሜታ የገለጹ ሲሆን የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትላቸውን አሉታዊ ተፅዕኖዎች ለመቋቋም የተገቡ ቃሎችን ወደ ተጨባጭ ተግባር መቀየር አስፈላጊ በመሆኑን በአፅንዖት ተናግረዋል።

በተጨማሪም ኢትዮጵያ በባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲ ላይ እምነትን የሚያጠናክር፣ ግልጽ፣ አካታች እና በአባል ሀገራት የሚመራ የኮፕ 32 ሂደትን ለመተግበር ያላትን ቁርጠኝነት በድጋሚ አረጋግጠዋል።
በይዘትና ድርድር፣ በሎጂስቲክስና ኦፕሬሽን፣ በአጋርነት እንዲሁም በሚዲያና ኮሙኒኬሽን ጨምሮ በተለያዩ ዘርፎች በዝግጅት ረገድ የተመዘገቡት ተጨባጭ እድገቶችንም አሳይተዋል።
ሎረን ፋቢየስ በበኩላቸው፤ በዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ መከላከል ላይ ታላቅ ስኬት የተመዘገበበትን የፓሪስ ስምምነት በማጽደቅ የተጠናቀቀውን ኮፕ 21ን የመሩበትን ልምድ አካፍለዋል።
በተጨማሪም ለኮፕ 32 በሚደረጉ ዝግጅቶች እንዲሁም ስኬታማ ጉባኤን ለማካሄድ አስተዋጽኦ ሊኖራቸው በሚችሉ ጉዳዮችና ካለፉት ጉባኤዎች በተገኙ ትምህርቶች እና ግንዛቤዎች ላይ የሁለቱ መሪዎች ውይይት ትኩረት ማድረጉን ከኮፕ 32 ኢትዮጵያ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡