በምክክር የጸናች ኢትዮጵያን ለትውልድ ማሻገሪያው ታሪካዊ ምዕራፍ

AMN- ሐምሌ 9/2018 ዓ.ም

ኢትዮጵያ የበርካታ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች፣ የባህል እንዲሁም የተለያዩ እምነት ተከታዮች በነፃነት የሚኖሩባት ሀገር ናት።

ቀደምት አባቶችና እናቶች ይህንን ውብ ልዩነት እንደ ትልቅ ጸጋና ውበት በመቀበል፣ መላው የጥቁር ሕዝቦች ኩራትና የነፃነት ተምሳሌት የሆነውን የአድዋ ድል በአንድነትና ባልተከፋፈለ ክንድ አስመዝግበዋል።

ይህ የአንድነትና የመደጋገፍ ታሪካዊ እሴት በዚህ ዘመን ተደግሞ፤ ከሕፃን እስከ አዋቂ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ባደረገው ንቁ ተሳትፎ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታን ለስኬት ለማብቃት ተችሏል።

አሁንም ሰላሟ የተረጋገጠ እና የበለጸገች ኢትዮጵያን ለቀጣዩ ትውልድ ለማሻገር ፍትሐዊ የባሕር በር ጥያቄን ጨምሮ አንድነትን የሚጠይቁ በርካታ ሃገራዊ ጉዳዮች አሉ።

ሆኖም የሀገሪቱ ታሪካዊ ጉዞ በርካታ ድሎችን ያስመዘገበ ቢሆንም፤ ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲንከባለሉ የመጡ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ልዩነቶች መኖራቸው አይካድም። እነዚህን ልዩነቶች በጥላቻና በጦርነት ሳይሆን በውይይትና በጠረጴዛ ዙሪያ ለመፍታት፣ ሀገራዊ ምክክር ወሳኝ መሆኑ ይታመናል።

በምክክር የጸናችና የተረጋጋች ሀገርን ለትውልድ ለማቆየት ታዲያ ላለፉት አራት ዓመታት በአካታችነትና በፍጹም ገለልተኝነት የአጀንዳ ልየታ ሂደት ተከናውኗል።

ለቀጣይ ሳምንታት የምክክሩ ተሳታፊዎች የኢትዮጵያ ሃገራዊ ምክክር ኮሚሽን ይፋ ባደረጋቸው ስምንት አበይት አጀንዳዎች ላይ በዝርዝር ይመክራሉ።

እነዚህም አጀንዳዎች ፤ የሀገር ግንባታ ጉዳይ ፣ የመንግስት አደረጃጃትና ስርአት ጉዳይ ፣ የፌዴራል ከተሞች አዲስ አበባ እና ድሬድዋ ከተሞች ጉዳይ፣ የሃይማኖት ጉዳዮች፣ የተቋማት ግንባታ የህግ የበላይነት እና ሰብዓዊ መብቶች ጉዳይ ፣ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እንዲሁም የአርሶ አደሮች እና አርብቶ አደሮች ጉዳዮች ፣ ሙስና እና የመልካም አስተዳዳር ጉዳዮች እና የሰላም ግንባታ ጉዳዮች ናቸው፡፡

የሃገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር መስፍን አርአያ (ፕ/ር) አጀንዳዎቹን ይፋ ባደረጉበት ወቅት እንደገለጹት፤ እነዚህ ስምንት አጀንዳዎች የመላው ኢትዮጵያውያን ድምፅ፣ ቅሬታ፣ ተስፋና ፍላጎት ውጤቶች ናቸው።

በዚህ ታሪካዊ የሃገራዊ ምክክር ጉባኤ ላይ ከመላ ሀገሪቱ የተውጣጡ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች የተወከሉ 4 ሺህ ተሳታፊዎች ከትላንት ጀምሮ እየመከሩ ይገኛሉ።

እነዚህ ተሳታፊዎች ከ130 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ የሚወክሉ በመሆናቸው ሀገራዊ አደራ ተጥሎባቸዋል።

በምክክሩ ላይ የሚሳተፉ ተውካዮች የወከሉትን ሕዝብ እውነተኛ ሐሳብና ፍላጎት በግልጽና በታማኝነት የማሰማት ታሪካዊ ኃላፊነትም አለባቸው።

ስለሆነም ይህንን ታሪካዊ ሃገራዊ ምክክር በመጠቀም፣ ለሀገራዊ መግባባት ቅድሚያ በመስጠት በምክክር የጸናች ኢትዮጵያን ለትውልድ ማሻገር ይገባል።

በትዝታ መንግስቱ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review