AMN – ሐምሌ 16/2018 ዓ.ም

ሕገ-ወጡ የሕወሓት ቡድን የትግራይ ክልል ሕዝብንና ተተኪውን ትውልድ ለከፋ አደጋና ጉስቁልና እየዳረገ መሆኑን የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችና የቀድሞ የሥራ ኃላፊዎች ገለጹ።
የትግራይ ዴሞክራቲክ ፓርቲ (ትዴፓ) ሊቀ-መንበር አረጋዊ በርሔ (ዶ/ር) እንደተናገሩት፤ ህገ-ወጡ የሕወሓት ቡድን ከተመሠረተበት ማግሥት ጀምሮ ችግሮችን በጠመንጃ አፈሙዝ ለመፍታት የሚሞክር ግትር አቋም ያለው የወንጀለኞች ስብስብ ነው።
በፕሪቶሪያ የተፈረመው የሰላም ስምምነት በተገቢው መንገድ ተግባራዊ እንዳይሆን እንቅፋት ሲፈጥር የቆየው ህገ-ወጥ ቡድኑ፤ በአሁኑ ወቅት ሰላማዊ የፖለቲካ አማራጮችን በመዝጋትና ከሻዕቢያ ጋር ያልተቀደሰ ጥምረት በመፍጠር የክልሉን ጊዜያዊ አስተዳደር በመፈንቅለ መንግሥት ማፍረሱን አክለዋል።
በተጨማሪም ወጣቶችንና ሕፃናትን ከቤተሰቦቻቸው በመንጠቅ ወደ ጦር ካምፕ በማስገባት ለተለያዩ አካላት የገቢ ምንጭ እያደረገ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
የፌዴራል መንግስት ለህገ-ወጡ ቡድን የሚያቀርበው ተደጋጋሚ የሰላም ጥሪና የሚያሳየው ትዕግሥት የሕዝቡን ጉስቁልና ለማስቀረት ያለመ መሆኑን አንስተዋል፡፡
የትግራይ ክልል የቀድሞው ርዕሰ መስተዳድር እና የዓረና ሉዓላዊነትና ዴሞክራሲ ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ ገብሩ አስራት በበኩላቸው፤ ህገ-ወጡ የሕወሓት ቡድን ሻዕቢያን ጨምሮ ከተለያዩ ህገ-ወጥ ኃይሎች ጋር በመጣመር የትግራይን ሕዝብ ለከፋ ጉዳት የሚዳርግ የጥፋት ተግባር ላይ በመሰማራት ጠላትነቱን በተጨባጭ ማረጋገጡን ተናግረዋል።
ቡድኑ ለሥልጣን ሲል ከክልሉ ሕዝብ ታሪካዊ ጠላቶች ጋር በመተባበር ለሌላ ግጭት እየተዘጋጀ እንደሚገኝ ጠቁመው፤ ሻዕቢያ የትግራይን ሕዝብ ለማጥፋት የሚጥር መሆኑን ቀደም ሲል በክልሉ የፈጸመው ጭፍጨፋና ያስከተለው ውድመት ማረጋገጫ ነው ብለዋል።
የቀድሞው የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤና የስምረት ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ የምክር ቤት አባል ኬርያ ኢብራሂም በሰጡት አስተያየት፤ ህገ-ወጡ የሕወሓት ቡድን የትግራይ ክልል ተተኪ ትውልድን ሆን ብሎ በመዋቅራዊ አሰራር እያጠፋና እያመከነ መሆኑን ገልጸዋል።
የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት የጥይት ድምፅ በማጥፋት ለክልሉ ሕዝብ ተስፋ የሰጠ ሁነኛ የሰላም በር ቢሆንም፣ ቡድኑ ስምምነቱን ለዳግም ጦርነት ጊዜ መግዣነት በመጠቀም የትግራይ እናቶችን እያስለቀሰ መሆኑን አስገንዝበዋል።
የመጀመሪያው የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ካቢኔ ሴክሬታሪያት ኃላፊ የነበሩት ፕሮፌሰር ክንደያ ገብረሕይወት በበኩላቸው፤ ሕገ-ወጡ የሕወሓት ቡድን የሰላም ስምነቱን በማፍረስ በትግራይ ክልል የሰብዓዊ መብት ረገጣውን እያጠናከረ መምጣቱን ነው ለኢዜአ የገለጹት።
ቡድኑ ወጣቶችን ለውክልና ጦርነት እየተጠቀመባቸው እንደሚገኝ ጠቁመው፤ ሕዝብን አሸብሮና አስገድዶ ወታደር የማድረግ ዓላማው ከሻዕቢያ የተኮረጀና በአሁኑ ወቅት በስፋት እየተተገበረ ያለ አደገኛ ድርጊት መሆኑን አስረድተዋል።