AMN- ሐምሌ 18/2018 ዓ.ም
ሚያዝያ 2025 ጄጄ ጋብሬል ለማንችስተር ዩናይትድ ከ18 ዓመት በታች ቡድን የመጀመሪያ ጨዋታውን አደረገ። ገና 14 ዓመቱ የነበረው ታዳጊ ዩናይትድ ሊድስን 13ለ1 ሲያሸንፍ ተቀይሮ በመግባት 25 ደቂቃ መጫወት ቻለ። በተሰጠው ደቂቃም ሁለት ግቦችን አስቆጥሮ በርካቶችን አስደመመ።
እንግሊዛዊው ባለተሰጥኦ እድሜው ገና ቢሆንም የ18 ዓመት በታች ቡድን ቋሚ አባል ሆነ። በአንዳንድ አጋጣሚዎች ለ21 ዓመት በታች ቡድኑም ጨዋታ ያደርግ ጀመር። በተለይ በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት ታዳጊው ለምን የበርካቶች መነጋገሪያ እንደሆነ አሳየ። ፍጥነቱ ፣ ቅልጥፍናው ፣ የመጀመሪያ የኳስ ንክኪው ፣ ተጫዋቾችን በቀላሉ የሚያልፍበት መንገድ እርሱን ደጋግሞ ማየትን ያስመኛል።
በተለይ በ2025/26 የውድድር ዘመን ለ18 ዓመት በታች ቡድኑ 32 ጨዋታዎች ላይ ተሳትፎ 29 ግቦችን ማስቆጠሩ ትኩረት በዛበት። የአውሮፓ ታላላቅ ክለቦች አይናቸውን ጣሉበት። የተጫዋቹን ሁኔታ በቅርበት በመከታታል ሊያስፈርሙት የሚችሉበትን ቀዳዳ አሰሱ። “ህፃኑ ሜሲ” የሚል ቅፅል ስም የተሰጠው ጋብሬል በተለይ ባርሰሎና በጥብቅ ተከታተለው።

ፕሮፌሽናል ውል የሚፈርምበት እድሜው ላይ ስላልደረሰ ዩናይትድ ተጫዋቹን በውል ማሰር አይችልም። የውድድሩ ዓመት እንደተጠናቀቀ ጄጄ ጋብሬል ልቡ ሸፈተ። ዩናይትድን መልቀቅ እንደሚፈልግ ፍንጭ አሳየ። ቀያይ ሰይጣናቱ ግን በእጃቸው ያለው ዕንቁ በቀላሉ መልቀቅ አልፈለጉም።
የክለቡ ፉትቦል ዳይሬክተር ጄሰን ዊልኮክስ ጣልቃ ገብተው ተጫዋቹን አሳመኑት። ለወኪሉ እና ቤተሰቡም ለተጫዋቹ እድገት አስፈላጊውን ሁሉ እንደሚያደርጉ ቃል ገቡ። ሩበን አሞሪም የዩናይትድ አሰልጣኝ በነበረበት ወቅት ለመጀመሪያ ጊዜ ከዋናው ቡድን ጋር ልምምድ መስራት ቻለ።
ተጫዋቹ ለዋናው ቡድን የመጫወት ፍላጎቱ ቢያድግም ዩናይትድ ግን ነገሮችን በጥንቃቄ መያዝ ፈልጓል። ደቃቃ ሰውነቱ መጎልበት አለበት ፤ ለዋናው ቡድን መጫወት የሚያመጣውን ጫና መቋቋም የሚያስችል ስነ ልቦና ማዳበርም ይጠበቅበታል።

ይህም ቢሆን ዘንድሮ በጨዋታ ላይ ባይሳተፍ እንኳን የዋናው ቡድን አካል ሆኖ ቢያንስ ተጠባባቂ ወንበር ላይ ይታያል ተብሎ ይጠበቃል። ይህንንም ትናንት ከኖርዌይ ክለብ ሮዘንበርግ ጋር በተከናወነው የአቋም መፈተሻ ጨዋታ ላይ ጀምሮታል።
የማንችስተር ዩናይትድ ደጋፊዎች በቀጣይ ጥቅምት ወር ላይ 16ኛ ዓመቱን ከሚይዘው ጄጄ ጋብሬል ብዙ ይጠብቃሉ። ዕድሜው ገና ቢሆንም ለዋናው ቡድን ሲጫወት ማየት የሚፈልጉ በርካታ ናቸው። ክለቡ ይህን ያደርግ ይሆን? በቀጣይ የአቋም መፈተሻ ጨዋታዎች ላይ እና የውድድር ዓመቱ በይፋ ሲጀመር የምንመለከተው ይሆናል።
በሸዋንግዛው ግርማ