የኢትዮጵያን ስር የሰደዱ ችግሮች በውይይት ለመፍታት እየመከርን ነው- የሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ተሳታፊዎች

AMN – ሐምሌ 19/2018 ዓ.ም

ኢትዮጵያውያን ስለ ሰላም ከፍ ባለ ድምፅ የሚያዜሙ፤ ሰላማቸውን ለማስጠበቅና ሀገራቸውን ለማፅናት የራሳቸውን ችግር በራሳቸው ለመፍታት የሚሞክሩ ሕዝቦች ናቸው።

ብሔራዊ ክብሯ የተጠበቀ፣ ሰላም የሰፈነባትና የበለጸገች ኢትዮጵያን ለትውልድ በማሻገር ሂደት ውስጥ የነዚያ ድርና ማግ ሆነው ስለ ሀገር ክብርና ፍቅር የተዋደቁ ልጆቿና በባህልና እሴት የታጠሩ ደጆቿ የማይፋቅ ደማቅ ታሪክን ጽፈው አልፈዋል።

ይሁን እንጂ ከጊዜ በኋላ የተፈጠሩ ልዩነቶችን ተከትሎ ከመነጋገርና መወያየት ይልቅ የጠመንጃ አፈሙዝ መማዘዝ አማራጭ እያደረጉ በወጡ የአብራኳ ክፋዮች የተነሳ ሀገሪቱ እንደ ቀደምትነቷ ሳትቀድም፣ እንደ ሀብቷም ሳትለማ ዘመናትን ለመሻገር ተገዳለች።

እነዚህ አለመግባባቶችን ለማረቅና ቅሬታዎችን በጠረጴዛ ዙሪያ ለመፍታትም የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ላለፉት አራት ዓመታት በጥልቀት ሲያከናውን የነበረውን ዝግጅት አጠናቆ ዛሬ ላይ የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ ደርሷል።

ከሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ መካሄድ በጀመረው በዚህ የምክክር ጉባኤ የተሳተፉ የሀገር ሽማግሌዎች ኢትዮጵያውያን ለዘመናት በጠንካራ ባህላዊ የግጭት መፍቻ ዘዴዎች ያለፉ ሕዝቦች መሆናቸውን አንስተው፣ ጠንካራ ሀገርን ለትውልድ ለማሻገር ምክክር አማራጭ የሌለው መፍትሔ መሆኑን ይናገራሉ።

ችግሮች ወደ ግጭት ከማምራታቸው በፊት በሰከነ መንፈስ የማየት፣ የመመርመር እና ዋጋ እንዳያስከፍሉ የማድረግ ባህላቸው አንዱ መገለጫቸው እንደሆነ ደግሞ በየብሔረሰቡ ያሉ ባህላዊ የዳኝነት ሥርዓቶች ሕያው ምስክሮች ናቸው።

የሀገራዊ ምክክሩ ተሳታፊ አቶ ተገኑ ረጋ፣ እርሳቸው የመጡበት ማህበረሰብ ከሌላ ቀርቶ ከራሱም ጋራ ቢጣላ የሚዳኝበት፣ ይቅር ለእግዚአብሔር የሚባባልበት የራሱ የሆነ ሕግ እንዳለው ይናገራሉ።

ልጆቻችን የእኛን መታረቅ፣ የእኛን መግባባት፣ ቅድሚያ ለሀገር የምንሰጥ መሆናችንን ካዩ የሚማሩና አስተዋዮች ይሆናሉ በማለትም ያስረዳሉ።

ሌላኛው የሀገራዊ ምክክሩ ተሳታፊ አጋዝ በለጠ ወልዴ፣ ሀገር ማለት ሰው ሲኖር ነው፣ ተራራና ወንዝ፣ ጫካ፣ ሜዳ፣ ሸለቆ ብቻ አይደለም፤ ሀገር ማለት ሰው ነው ያሉ ሲሆን፣ ሰው ማለት ደግሞ እኔ፣ አንተ፣ አንቺ፣ ሁላችንም ማለት ነው ሲሉ ያብራራሉ።

ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን የምንባለው ስንኖር ነውና ስለዚህ በዚህ መልኩ ስንመካከር ችግሮቻችንን መፍታት እንችላለን ብለዋል።

መሣሪያ ከመሳብ ጠረጴዛ ስቦ ቁጭ ብሎ ምንድን ነው ያንተ ችግር? ምንድን ነው ያንቺ ችግር? በመባባል ብንነጋገር መፍታት እንችላለን ሲሉም አክለዋል።

ሌላው የሀገራዊ ምክክሩ ተሳታፊ ሻምበል አለማየሁ ታፈሰ፣ ትውልድን፣ ሀገርን ማስቀጠል የሚቻለው በመመካከር መሆኑን ይናገራሉ።

ለትውልድ ጭቅጭቅን እና ሌሎች ባዕድ የሆኑ ነገሮችን ሳይሆን፣ ቁጭ ብሎ በመመካከር ጥሩ የሆነውን ነገር ማስተላለፍ እንደሚገባም ይገልፃሉ።

ይህ ትውልድ መታረቅን፣ መከባበርን፣ መወያየትን፣ መግባባትን መለማመድ እንደሚገባውም ያስገነዝባሉ።

የሀገራዊ ምክክር ጉባኤው ተሳታፊዎች አክለውም፣ የምክክር ጉባኤው ሀሳቦችንና ልዩነቶችን ወደ ጠረጴዛ በማምጣት ያለ ምንም አድሎና ተጽዕኖ በመከባበርና በመደማመጥ እየተካሄደ እንደሚገኝም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

በታምራት ቢሻው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review