ዜጎች ይመክራሉ ኢትዮጵያ ትድናለች-የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን

AMN ሐምሌ 19/2018 ዓ.ም

ሀገር በብርቱ ዜጎቿ ጥረት የምትገነባ የጋራ ቤት ናት።የጋራ ቤታችን ኢትዮጵያን በጸና አለት ላይ መገንባት ለቀጣዩ ትውልድ የተረጋጋ ማኅበራዊ ቁርኝትን ይፈጥራል።ምክክርን ባሕል ማድረግ ደግሞ ሰላምን አንግሦ ሀገራዊ መግባባትን ያጠናክራል።

ኢትዮጵያዊያን የጋራ ቤታቸውን ሊያጸኑ፣ ማኅበራዊ ውላቸውንም ሊያንጹ የሀሳብ የበላይነትን ማዕከል አድርገው እየተመካከሩ ነው።

በምክክር ጉባኤው በርካታ አመለካከቶች በምክንያት እየቀረቡ ነው።ተቃራኒ ሀሳቦች በአመክንዮ እየተስተናገዱ ነው። አንዱ የሌላውን ብሶት እያዳመጠ ቀስ በቀስ የመግባባት ጎዳና እየተጠረገ ነው።

በእርግጥም ኢትዮጵያዊያን በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በሰላማዊ መንገድ መነጋገር እንደሚችሉ በተግባር እየታየ ነው። ኢትዮጵያ መሸከም የማትችለው ግጭትና አለመግባባትን እንጂ መመካከርን እንዳልኾነ ልጆቿ እያስመሰከሩ ነው። የኢትዮጵያ ልጆች እናት ሀገራቸውን በሀሳብ ተዋፅኦ ሊያጸኑ ብዕር፣ ወረቀትና አዕምሯቸውን አሰናድተው በመመካከር ላይ ናቸው።

ያለመግባባት መንስኤዎች ተለይተው የመፍትሔ ሀሳቦች ሲቀርቡ ሀገራችንን ያሳመሙ ሰንኮፎች አንድ በአንድ ይወገዳሉ። በምክክር ጉባኤው ላይ እየታየ ያለው እውነታም ይኸው ነው። ኢትዮጵያዊያን የመንግሥት አስተዳደርን፣ ማኅበራዊ ቁርኝትን፣ ኢኮኖሚያዊ ሁኔታን፣ ፍትሕና ርትዕን የተመለከቱ ቁልፍ ሀገራዊ ጉዳዮችን አንስተው መወያየታቸው በዘላቂነት የሀገር ባለቤትነት ስሜታቸውን እንደሚያጠናክር ይጠበቃል።

ተመካካሪዎች የሀሳብ ገደብ የለባቸውም። የልባቸውን አውጥተው ለመናገር ቋንቋም አያግዳቸውም።ኹሉም በሚችለው ቋንቋ ሀሳቡን እየገለጸ ነው። የሚነሱ ሀሳቦች በርካታ ቢኾኑም ማዕከላቸው ሀገር ነው። ኢትዮጵያችን በልጆቿ ምክክር ሕመሞቿን የምታድንበት ጉባኤ አካታችነትን፣ መደማመጥን እና አመክንዮን አንግቦ እየተጓዘ ነው።

ዜጎች የሀገር ባለቤትነታቸው በተግባር የሚረጋገጠው በወሳኝ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ተሳትፎ ሲያደርጉ ነው። ሀገራዊ የምክክር ጉባኤው ኢትዮጵያዊያን በጋራ አስተሳስረው የሚያኖሯቸውን ሕጎች፣ አሠራሮች፣ አደረጃጀቶች፣ የሀሳብ መሠረቶች የሚያድሱበት ብሎም የሚነድፉበት በመኾኑ ኢትዮጵያን ያክማታል። ኢትዮጵያን ያሳመማት አለመግባባት፣ የሚያክሟት ደግሞ ዜጎቿ ናቸው።

በዜጎች ልባዊ ምክክር ኢትዮጵያ ከሕመሟ ትድናለች!

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review