AMN- ሐምሌ 20/2018 ዓ.ም

በአዲስ አበባ ከተማ ባለፉት አምስት ዓመታት በቱሪዝም ዘርፍ በተከናወኑ ሥር ነቀል መዋቅራዊ እና ተቋማዊ ለውጦች የከተማዋ ገጽታ በመቀየሩ ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ ቱሪስቶች ቁጥር ከፍተኛ ዕድገት አሳይቷል።

መንግሥት ለዘርፉ በሰጠው ትኩረት እና ባከናወናቸው ሰፋፊ የመዳረሻ ልማት ሥራዎች ከተማዋን ቀዳሚ የቱሪስት መዳረሻ ማድረግ የተቻለ ሲሆን በዚህም የአገር ውስጥ ጎብኚዎች ቁጥር ከነበረበት 4 ነጥብ 1 ሚሊየን ወደ 10 ነጥብ 5 ሚሊየን ከፍ ብሏል፡፡

ከተማዋን የጎበኙ የውጭ ቱሪስቶች ቁጥር ከነበረበት 123 ሺህ 489 በአምስት አመታት ውስጥ ወደ 1 ነጥብ 2 ሚሊየን አድጓል፡፡
ባለፉት ዓመታት በአዲስ አበባ ከተማ የተከናወኑ መዋቅራዊ እና ተቋማዊ ለውጦች የከተማዋን ገጽታ ከመቀየር ባለፈ ዓለም አቀፍ የቱሪስት ፍሰት በከፍተኛ ደረጃ እንዲጨምር አድርጓል፡፡

የቱሪዝም ሴክተሩን በብቃት ለመምራት የተዘረጉ ተቋማዊ ማሻሻያዎች እና የዲጂታል አሰራሮችም ዓለም አቀፍ ጎብኚዎች ያለእንግልት አገልግሎት እንዲያገኙ አስችለዋል፡፡
የከተማዋን ውበት የሚጨምሩ እንደ የኮሪደር ልማት ስራዎች፣ አዳዲስ የተገነቡ መናፈሻዎች እና ሁለገብ አረንጓዴ ልማት ሥፍራዎች የሀገር ውስጥ እና የውጭ ቱሪስቶችን ትኩረት ስበዋል።
ዓለም አቀፍ ጉባኤዎች፣ የኮንፈረንስ ቱሪዝም እና ዲፕሎማሲያዊ ጉዞዎችን ይበልጥ ማጠናከር መዲናዋን የቱሪዝም ማዕከል እያደረጓት ይገኛል።
በበረከት ጌታቸው
See less