AMN- ሐምሌ 22/2018 ዓ.ም
ኢትዮጵያውያን ለአንድ የጋራ ዓላማ በአንድነት በመቆም በአንድ ጀምበር 800 ሚሊየን ችግኞችን ለመትከል ዝግጅታቸውን አጠናቀዋል።
ዜጎች በአንድ ጀምበር 800 ሚሊየን ችግኞችን የመትከል መርሐ ግብርን የሚያከናውኑት ሐምሌ 27 ቀን 2018 ዓ.ም ነው፡፡
በዘንድሮው የክረምት ወቅት «ተስፋን እንትከል» በሚል መሪ ሃሳብ እየተካሄደ የሚገኘው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር በከፍተኛ ህዝባዊ ተሳትፎ እየተከናወነ ሲሆን ይህም የኢትዮጵያውያንን የጋራ ህልምና የተቀናጀ ክንድ ለዓለም የሚያሳይ ነው።
ኢትዮጵያውያን ባለፈው ዓመት በመላ ሀገሪቱ 700 ሚሊየን ችግኞችን በአንድ ጀምበር በመትከል በዓለም አቀፍ ደረጃ ታሪክ መስራታቸው ይታወሳል።
የዘንድሮው በአንድ ጀምበር 800 ሚሊየን ችግኞች ለመትከል የተያዘው እቅድ ደግሞ ይህንን ሀገራዊ ስኬት ወደ ላቀ ደረጃ በማሸጋገር፣ የህዝቡን የጋራ አንድነትና ለአካባቢ ጥበቃ ያለውን ቁርጠኝነት ዳግም የሚያስመሰክር ይሆናል።
ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ በተተገበረው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ከ48 ቢሊየን በላይ ችግኞች በመላ ሀገሪቱ የተተከሉ ሲሆን በዚህም የሀገሪቱ የደን ሽፋን ወደ 23.6 በመቶ ሊያድግ ችሏል፡፡
በዘንድሮው የክረምት ወቅት በአጠቃላይ ከ8 ቢሊየን በላይ ችግኞችን ለመትከል ታቅዶ በስፋት እየተከናወነ ሲሆን በአዲስ አበባ ብቻ ዘንድሮ 6 ሚሊየን ችግኞችን ለመትከል ከታቀደው ውስጥ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ከ4 ሚሊየን በላይ ችግኞች ተተክለዋል።

የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር በቀጥታ ከሀገሪቱ የረጅም ጊዜ የልማት ግቦች ጋር የተያያዘ በመሆኑ የአፈር እና የውሃ ጥበቃ ስራዎችን ማጠናከር፣ የመስኖ አጠቃቀምን በማስፋፋት የሀገሪቱን የምግብ ዋስትና ማረጋገጥ እንዲሁም ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ሊስማሙ የሚችሉ ዘመናዊ የግብርና አሰራሮችን አካቷል፡፡
ኢትዮጵያ እያከናወነችው የሚገኘው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ከሀገር አልፎ ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት መልካም ተሞክሮ እየሆነ ይገኛል።
በአዲስ አበባ የሚኖሩ የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ አባላት እና ዓለም አቀፍ ተቋማትም የዚህ ታላቅ ሀገራዊ እንቅስቃሴ አካል በመሆን አሻራቸውን በማሳረፍ ላይ ናቸው።
በዚህም ሐምሌ 27 ቀን 2018 ዓ.ም ኢትዮጵያውያን በነቂስ በመውጣት የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትለውን ጉዳት ለመቀነስ፣ ሥነ-ምህዳሩን ለመታደግ እና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በሚደረገው በዚህ ታሪካዊ መርሐ ግብር የአረንጓዴ ዐሻራቸውን በማሳረፍ እንዲሳተፉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጥሪ አቅርበዋል።
በትዝታ መንግስቱ