አፍሪካ ያላትን የተፈጥሮ ሀብት ከብሪክስ አባል ሀገራት አቅም ጋር ማቀናጀት ይገባል – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)

AMN – መስከረም 3/2019 ዓ.ም

በህንድ አስተናጋጅነት በተካሄደው የብሪክስ መሪዎች ጉባኤ ላይ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፤ አፍሪካ ያላትን እምቅ የተፈጥሮ ሀብት ከብሪክስ አባል ሀገራት ካፒታል፣ ቴክኖሎጂ እና ገበያ ጋር በማቀናጀት እሴት መፍጠር እንደሚገባ አሳሰቡ።

የአፍሪካን የተፈጥሮ ሀብት ከብሪክስ አባል ሀገራት አቅም ጋር በማስተሳሰር ሰፊ አጋርነት መፍጠር እንደሚገባ የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)፤ ኢትዮጵያ በማዕድናት፣ በታደሽ ኢነርጂ እና በዲጂታል ኢኮኖሚ እነዚህን አጋርነቶች ለመገንባት ዝግጁ መሆኗን ገለጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በንግግራቸው፤ የብሪክስ ጥንካሬ በእያንዳንዱ ሀገር በሚያመጣው አበርክቶ ላይ የተመሰረተ መሆኑን የገለጹት ሲሆን፣ ለኢነርጂ ሽግግር፣ ለላቀ ማምረቻ እና ለዲጂታል ኢኮኖሚ መሠረት የሆኑት ማዕድናት ለዚህ ጥሩ ማሳያ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

አፍሪካ ከእነዚህ ሀብቶች ውስጥ እጅግ ብዙዎቹን ባለቤት መሆኗን ገልጸው፣ እድሉ እነሱን አንድ ላይ በማምጣት ሰፊ አጋርነትን መፍጠር እንደሆነ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በማዕድናት፣ በታደሽ ኢነርጂ እና በማደግ ላይ ባለው የኢንዱስትሪ መሠረት ላይ በመመስረት እነዚህን አጋርነቶች ለመገንባት ዝግጁ መሆኗን ገልጸዋል።

ከዚህም በተጨማሪ ኢትዮጵያ አፍሪካን ከዓለም ጋር የሚያገናኘው የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ጎረቤት ኢኮኖሚዎችን እያገለገለ ያለው የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት፣ እና የአፍሪካ ሕብረት መዲና የሆነችው አዲስ አበባ ለሰፊ አጋርነት ምቹ መድረኮች መሆናቸውን አንስተዋል።

ለዚህም ሲባል አፍሪካ ከ«አጀንዳ 2063» ጋር በተሻለ ሁኔታ እንድትጣጣም ኢትዮጵያ በብሪክስ እና በአፍሪካ ሕብረት መካከል ጠንካራ ምክክር እንደሚኖራት እንደምትደግፍ ገልጸዋል።

በፍሬሕይወት ብርሃኑ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review