AMN- ሐምሌ 24/2018 ዓ.ም

በአማራ ክልል የሰኔ 15ቱ ክስተት በሀገራችን የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ ትልቅ ጥቁር ጠባሳ ጥሎ አልፏል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
የሰኔ 15ቱን መጥፎ ክስተት በተመለከተ ማብራሪያ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ታሪክን ማዛባት ለነገው ትውልድ የሚተርፍ እዳ ነው ብለዋል።
ለውጥን ለማምጣት በጽናት ሲሰሩ የነበሩ የለውጥ አበጋዞችን ያጣንበት፣ በፖለቲካው መካከል የመተማመን መንፈስ እንዲሸረሸር ያደረገ እና የስልጣን ሽሚያ በሃይል የማስከበር መጥፎ ባህልን ያስቀጠለ አጋጣሚ እንደነበርም ገልጸዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) ስለ እለቱና ስለተፈጠረው ክስተት ሲያብራሩ፤ እለቱ ቅዳሜ ነበረ፤ መረጃውን እንደሰማሁ ለህዝብ መግለጫ እንዲሰጥ ሚዲያዎች እንዲጠሩ አደረግኩ፤ ፋና እና ኢቢሲ በምሽቱ ፈጥነው አልደረሱም ነበር፤ አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ግን እዚሁ 4 ኪሎ አቅራቢያ ስለነበር በፍጥነት ደረሰ ብለዋል።
መግለጫውን እኔ ቤት ሆኜ ለአሚኮ ሰጠሁ፤ በኋላ ግን ‘ባህር ዳር ሆኖ መግለጫ ሰጠ’ ተብሎ የሴራ ትንተና ተፈበረከበት በማለት አስታውሰዋል።
ይህ ክስተት ያስተማረን ትልቅ ሀቅም ታሪክን በትክክል አለማስቀመጥና ማዛባት ለዛሬ ብቻ ሳይሆን ለነገውም ትውልድ እዳ ያተርፋል ሲሉ ተናግረዋል።
ገዳይም ሟችም በአንድ ላይ ‘ጀግና’ የሚደረግበት የታሪክ ስብራት ሊቆም እንደሚገባም በአፅንኦት አስገንዝበዋል።
በታምራት ቢሻው