የአዲስ አበባ ሕብረተሰብ ተሳትፎና በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ኮሚሽን የዲጂታል በጎነት ፕሮጀክት አስጀመረ

You are currently viewing የአዲስ አበባ ሕብረተሰብ ተሳትፎና በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ኮሚሽን የዲጂታል በጎነት ፕሮጀክት አስጀመረ

AMN – ሐምሌ 25/2018 ዓ.ም

ፕሮጀክቱን ያስጀመሩት የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ እና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጃንጥራር አባይ፤ መዲናዋ እያካሄደች ባለው የልማት እንቅስቃሴ የሚያለቅሱ እናቶችን እንባ ያበሰ እና ልትጠፋ የነበረችን ነፍስ ያዳነ ታላቅ ስራ መከናወኑን ገልጸዋል።

ምክትል ከንቲባው አክለውም፣ በተጀመረው የዲጂታል ሀብት ማሰባሰቢያ ፕሮጀክት ቀና ልብ ያላቸው ኢትዮጵያውያን ንቁ ተሳትፎ በማድረግ በጎነትን ሊያጎለብቱ እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል።

የአዲስ አበባ ሕብረተሰብ ተሳትፎና በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ኮሚሽን ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር በመተባበር በአጭር የጽሑፍ መልዕክት ገቢ የሚሰበሰብበትን የዲጂታል በጎነት ፕሮጀክት ማስጀመሩን አስታወቀ።

በ6400 ‘A’ አጭር የጽሑፍ መልዕክት ሕብረተሰቡን በማሳተፍ ሀብት የሚሰበሰብበት ይህ ዲጂታል አማራጭ፣ በመልካም ተሞክሮነት የመረዳዳት ባህልን በማህበረሰቡ ዘንድ የማስረጽ ዓላማን የያዘ እንደሆነ ተገልጿል።

የኮሚሽኑ ኮሚሽነር አቶ ይመር ከበደ እንደገለጹት፣ ፕሮጀክቱ በ6400 ‘A’ አጭር የጽሑፍ መልዕክት በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ 1 ሚሊዮን ቤተሰቦችን በማፍራት 360 ሚሊዮን ብር የመሰብሰብ እቅድ አለው። አክለውም የዛሬው ጥቃቅን መዋጮ የነገ ግዙፍ ፕሮጀክቶች መገንቢያ መሠረት እንደሚሆን አስረድተዋል።

ፕሮጀክቱ ከበጎ ፈቃደኞች በቀን አንድ ብር ወይም በወር 30 ብር የመሰብሰብ እቅድ ያለው ሲሆን፣ የሚገኘው ገቢም የአቅመ ደካሞችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች በሚያቃልሉ ፕሮጀክቶች ላይ የሚውል ይሆናል።

በፈቃዱ መለሰ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review