AMN- መስከረም 10/2019 ዓ.ም

የበርካታ ብሔር ብሄረሰቦች፣ ሃይማኖቶች፣ ባህሎች፣ ቋንቋዎችና ማንነቶች መገኛ የሆነችዉ ኢትዮጵያ በሃገር አቀፍ ደረጃ በየአመቱ መስከረም አንድ አሮጌዉን አመት ሸኝታ አዲሱን ዘመን ትቀበላለች፡፡
በዘመን መለወጫዉ መዳረሻ እና በበአሉ ዕለት የሚከበሩት እንደ አበባ አየሽ ወይ ጎቤ፣ ሽኖዬ፣ አሸንዳ፣ አሸንድዬ፣ ሶለል ያሉ ወጣት ወንዶችና ሴቶች ብቻ የሚሳተፉባቸዉ ጭፈራዎችና ጨዋታዎች የአዲስ አመት ድምቀቶች ናቸዉ፡፡

የመስቀል ደመራ በአል አዲስ አበባን በአብዛኛዉ የሃገሪቱ ክፍሎች የሚከበር ሃይማኖታዊ በአል ሲሆን ዋንኛ የመስከረም ወር ድምቀት ነዉ፡፡
ኢትዮጵያ በብዝሃነት የደመቀች ሃገር እንደመሆኗ መጠን በሃገሪቱ የሚገኙ የተለያዩ ብሄር ብሔረሰቦች እና ሃይማኖቶች መስከረም አንድ ከሚያከበረዉ የዘመን መለወጫ በአል ጎን ለጎን የየራሳቸዉን የዘመን መለወጫና የምስጋና ቀን በተለየ ሁኔታ ያከብራሉ፡፡

የኦሮሞ ህዝብ የምስጋና በአል “ኢሬቻ “፣ የጌዲኦ ብሄር የዘመን መለወጫ በዓል “ደራሮ”፣ የጎፋ ዘመን መለወጫ በአል “ጋዜ መስቃላ”፣ የኦይዳ ብሄር ዘመን መለወጫ በአል “የአ ማስቃላ”፣የሲዳማ ዘመን መለወጫ በአል “ፍቼ ጨምበላላ”፣ የሃላባ ብሔረሰብ ዘመን መለወጫ “ሴራ” መንገሳ”፣ የአሪ ብሔረሰብ ዘመን መለወጫ “ድሽታ ግና”፣ የዳዉሮ ብሔረሰብ ዘመን መለወጫ “ቶኪ-በዓ” በተለያዩ የብሄር ብሄረሰቦች የሚከበሩ በአላት ናቸዉ፡፡
የኮንታ ብሔረሰብ ዘመን መለወጫ ‘ህንግጫ’፤ የወላይታ ብሄር የዘመን መለወጫ “ጊፋታ”፤የቡርጂ ብሔር የዘመን መለወጫ “ዎናንካ አያና”፤ የጉሙዝ ዘመን መለወጫ በዓል “ጓንዷ”፤የጋሞ ብሔረሰብ ዘመን መለወጫ “ዮዮ ማስቃላ”፤ የሀዲያ ዘመን መለወጫ “ያሆዴ “፤ የቦሮ ሺናሻ አዲስ አመት “ጋሪዎሮ”፤ የካምባታና ጣምባሮ ብሄረሰብ ዘመን መለወጫ “ማሳላ”፤ የካፈቾ ብሔር ዘመን መለወጫ “ማሽቃሮ”፤ የየም ብሔረሰብ ዘመን መለወጫ “ሄቦ”፤ የዘይሴዎች ዘመን መለወጫ “ቡዶ ኬሶ”፤ የጊድቾዎች ዘመን መለወጫ “ባላ ካዳቤ እና ሌሎች በአላት የኢትዮጵያ ድምቀቶች ናቸዉ፡፡

ሁሉም በአላት በአብሮነት፣ በወንድማማችነት፣ በይቅርታና በመተሳሰብ የሚከበሩ መሆናቸዉ የኢትዮጵያን ህብረብሄራዊ አንድነት የሚያረጋግጡ ናቸዉ፡፡
በእነዚህ በአላት ላይ የሚቀርቡት ባህላዊ ምግቦችና መጠጦች፣ አልባሳት፣ ጭፈራዎች እና ሌሎች ባህላዊ ስነ ሥርዓቶች የኢትዮጵያዊነት ልዩ መገለጫዎች ናቸዉ፡፡
ኢትዮጵያዊያን በአብዛኛዉ እነዚህን በአላት የሚያከብሩት ጭጋጋማዉና አስቸጋሪዉ የክረምት ወቅት አልፎ ምድር በልምላሜ በምታጌጥበት ወቅት መሆኑ ደግሞ አዲሱ አመት በምስጋና፤ በተስፋ እና በመልካም ምኞት የታጀበና የደመቀ እንዲሆን ያደርገዋል፡፡
በወንድማገኝ አሰፋ