አዲስ አበባ በአረንጓዴ ትራንስፖርት ጉዞዋ የካርበን ልቀትን በከፍተኛ ደረጀ መቀነስ ችላለች

You are currently viewing አዲስ አበባ በአረንጓዴ ትራንስፖርት ጉዞዋ የካርበን ልቀትን በከፍተኛ ደረጀ መቀነስ ችላለች

AMN – መስከረም 8/2019 ዓ.ም

በነዳጅ ጥገኛ በነበረው የከተማዋ የትራንስፖርት ሥርዓት ሳቢያ ለአየር ብክለት ምክንያት ሆኖ የነበረው ከፍተኛ መጠን ያለው አማቂ ጋዝ፣ በታዳሽ ኃይል እና በኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች መተካቱ ተገለጸ።

ከተማ አስተዳደሩ ሞተር-አልባ የትራንስፖርት አማራጮችን በማስፋፋት እና የኤሌክትሪክ አውቶቡሶችን አገልግሎት በማጠናከር አረንጓዴውን የልማት ራዕይ በተግባር እየፈተሸ ይገኛል።

የአዲስ አበባ ከተማ ትራንስፖርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ አስምሮም ብርሃኔ፣ የዘርፉ የበካይ ጋዝ ልቀት ከፍተኛና አሳሳቢ ደረጃ ላይ የነበረ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ከአጠቃላይ የከተማዋ ብክለት ውስጥ 32 በመቶውን ድርሻ እንደሚይዝም ተናግረዋል።

ቢሮው ከልማት አጋሮች ጋር በመተባበር በከፍተኛ የፍሰት ሰዓቶች በአየር ጥራት መቆጣጠሪያ 16 አካባቢዎች መሣሪያዎችን መገጠሙን ገልጸው፣ የተገኙት መረጃዎችም አስደንጋጭ እንደነበሩ አንስተዋል።

ከተማዋን ወደ ግሪን ትራንስፖርት ለማሸጋገር በነዳጅ የሚሠሩ ተሽከርካሪዎችን በመቀነስ ወደ ኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች መግባት እና ሞተር-አልባ የትራንስፖርት አማራጮችን ማስፋፋት ዋና ዋና የተከናወኑ ሥራዎች መሆናቸውን አብራርተዋል።

በሥራ ላይ የዋሉት የመጀመሪያዎቹ መቶ የኤሌክትሪክ አውቶቡሶች በከተማዋ ትራንስፖርት ላይ የፈጠሩትን በጎ ለውጥ በማሳየት፣ ከተማ አስተዳደሩ ተጨማሪ የኤሌክትሪክ አውቶቡሶችን ለመግዛት በሂደት ላይ መሆኑን ጠቁመዋል።

የአካባቢ ጥበቃ ባለሙያው አቶ ሰለሞን መለሰ በበኩላቸው፣ የቤንዚን እና የናፍታ ተሽከርካሪዎች ከፍተኛ ሙቀት የሚፈጥሩና ከባቢ አየርን የሚበክሉ ጋዞችን እንደሚለቁ ገልጸዋል።

በትራንስፖርት ሴክተሩ ብቻ ይለቀቅ ከነበረው ሁለት ሚሊዮን አምስት መቶ ሺህ ቶን አማቂ ጋዝ ውስጥ፣ በዚህ ዓመት ብቻ 384 ሺህ ሜትሪክ ቶን ካርቦን ዳይኦክሳይድ መቀነስ መቻሉን ተናግረዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ምክትል ኃላፊ አቶ አዱኛ ወንድሙ፣ ቀደም ሲል ሞተራቸው ከፍተኛ የካርበን ልቀት ይለቁ የነበሩ ተሽከርካሪዎች መኖራቸውን አስታውሰዋል።

ይሁን እንጂ የሳይክል እና የእግረኛ መንገዶች መዘርጋት እንዲሁም ተቋማት ውስጥ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ መሙያ (ቻርጅንግ) ቦታዎች መዘጋጀታቸውን ጨምሮ ከ2016 ዓ.ም ጀምሮ ከተከናወኑ ተራማጅ ሥራዎች ጋር ተደማምሮ ወደ ከባቢ አየር ይለቀቅ የነበረው 965 ሺህ 442 ሜትሪክ ቶን ካርቦን ዳይኦክሳይድ መቀነስ ተችሏል ብለዋል።

በከተማዋ እየተተገበሩ ያሉት አረንጓዴ የትራንስፖርት አማራጮች በተለይም የስኩተር እና የሳይክል አገልግሎቶች ፈጣን፣ ምቹ እና ከትራፊክጨናነቅ ነጻ የሆነ ጉዞ እንዲኖር በማድረግ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከቱ መሆኑን ተጠቃሚዎችና አከራዮች ተናግረዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከግለሰብ ተሽከርካሪዎች እስከ ብዙሃን ማጓጓዣ አውቶቡሶች በታዳሽ ኃይል እንዲሠሩ ማድረግ፣ ወጪን መቀነስ እና ከባቢ አየርን መጠበቅ የሚያስችሉ የኢኮ-ትራንስፖርት መሠረተ ልማቶችን ማስፋፋቱን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጿል።

በፍሬሕይወት ብርሃኑ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review