AMN ሐምሌ 27/2028

በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር የምንተክለው ችግኝ ለሀገር ዕድገት መሰረትና ለትውልድ የሚሻገር ተስፋ ነው ሲሉ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ ታገሰ ጫፎ ገለጹ፡፡
“ተስፋን እንትከል” በሚል መሪ ሀሳብ የሚካሄደው የአንድ ጀምበር 800 ሚሊዮን ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ከንጋቱ 12 ሰዓት ጀምሮ እየተካሄደ ይገኛል፡፡
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ ታገሰ ጫፎ በአንድ ጀምበር የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ዐሻራቸውን አኑረዋል፡
አፈ-ጉባዔ ታገሰ ጫፎ በዚሁ ወቅት፤ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር እጅግ ስኬታማ በሆነ መንገድ እየተከናወነ ነው ብለዋል፡፡
የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ትውልድ የሚሻገር ሀገር የሚገነባ ራዕይ መሆኑን ጠቅሰው ፈጣን ልማትን ለማረጋገጥ ትልቅ መሳሪያ ሆኖ እያገለገለ መሆኑን ገልጸዋል።
ባለፉት ሰባት ዓመታት በተከናወነው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የደን ሽፋን ከነበረበት 17 ነጥብ 3 በመቶው ወደ 23 ነጥብ 6 በመቶ ከፍ ማለት መቻሉን ጠቁመዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት ትልቅ ለውጥ እየመጣ መሆኑን አንስተው፤ ቡናን ጭምሮ የግብርና ምርትና ምርታማነት እጅጉ እያደገ መምጣቱን ጠቅሰዋል፡፡
የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብሩ የውሃና ተፈጥሮ ሀብቶች እንዲያገግሙ፣ ወንዞችና ሀይቆች እንዲለመልሙ እንዲሁም ለዱር እንስሳት የተመቸ ስፍራ እንዲኖር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን አመላክተዋል፡፡
የአንድ ጅምበር 800 ሚሊዮን የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር እቅድ እውን እንዲሆን መላ ኢትዮጵያውያን ርብርባቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡