
”የጠላቴ ጠላት ወዳጄ ነዉ” በሚል መርህ እየተመራ ከዉስጥም ከዉጭም ሃሳብ አልባ ኃይል ያሰባስባል፡፡
ከዉስጥ ቅሬታን አባብሶ ኃይልን ለማሰባሰብ አራት መንገዶችን ይጠቀማል፤ በሃገረ መንግስቱ የተፈጠሩ ፈተናዎችን፤ አንድ ሕዝብ ከሌላ ሕዝብ ጋር ፈጥሮታል ብሎ የሚነዛዉን በደል፤ በአንድ ሕዝብ መካከል ያሉ ንዑሳን ማንነቶችን በቅሬታ ማነሳሳት፤ እና በአንድ ማሕበረሰብ መካከል ተጠቃሚና ተጎጂ፤ ጨቋኝና ተጨቋኝ፤ ገዥና ተገዢ ፤ ዓይነት መደቦችን በመፍጠር፡፡
ከዚህ ባለፈ በተስፋና በገንዘብ እየተሳቡ እንዲቀላቀሉ የሚጋበዙ ኃይሎች ይኖራሉ፡፡
ከሃገር ዉጭ ደግሞ በሶስት መንገዶች አጋር ይገዛል፤ በሃገር ጥቅም ላይ ቆሞ አጋር በመፈለግ፤ የሎጅስቲክስና የፖለቲካ ሽፋን የሚሰጥ ኃይልን በመሳብና በማብዛት፤ እንዲሁም በባንዳነት ለዉጭ ኃይል በማገልገል፡፡
በቅራኔ ተሰባስቦ በአጋር አይዞህ ባይነት የበዛዉ ኃይል ወደ ቀጣይ ሦስተኛዉ ዕድገት ደረጃ በማደግ፤ በሐሳብ አልባ የፖለቲካ ምኅዳር ዉስጥ አስቻይ ዐቅሞችን ወደ መዘርጋት ይሻገራል፡፡
የተቀጣጠለዉንና የበዛዉን ኃይል በሥርዓት ለማንቀሳቀስ የሚያስችል ዐቅም ለማጎልበት አስቻይ መደላድሎችን መዘርጋትና ማሣለጥ ግብ አድርጎ ይሰራል፡፡
ይህንን ግብ ለማሳካት በዚህ ደረጃ ሁለት መሰረታዊ እንቅስቃሴዎች ይታያሉ፡፡
የመጀመሪያዉ ግልጽና ኅቡዕ መዋቅሮች ናቸዉ፡፡ ሁለተኛዉ ደግሞ ገንዘብ ነዉ፡፡ – የመደመር መንግሥት ገጽ – 362