ኢትዮጵያውያን ለልጆቻቸው መሰረት ለመጣል ሲወስኑ ምን ማድረግ እንደሚችሉ ለዓለም ህዝብ አሳይተዋል – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

AMN- ሐምሌ 27/2018 ዓ.ም

ኢትዮጵያውያን ለልጆቻቸው መሰረት ለመጣል ሲወስኑ ምን ማድረግ እንደሚችሉ ለዓለም ህዝብ አሳይተዋል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሰጡት መግለጫ እንዳሉት፤ ውሏችን ኢትዮጵያውያን ሲወስኑ ለነገ ለልጆቻቸው ተስፋን መትከል እንደሚችሉ ዛሬ ዳግም ለዓለም ህዝብ ያሳየንበት ቀን ነው፡፡

ይሄንን ታላቅ ተግባር ለፈጸመው የኢትዮጵያ ህዝብ ምስጋና ያቀረቡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በዚሁ መልክ ተደምረን ተስፋን በመትከል የነገይቱን ኢትዮጵያ የምትበልጽግ፣ የምትለማ እና የማትለምን እንዲሁም ለተቸገሩ የምትደርስ መሆኗን ለአፍሪካ፣ ለዓለም ማሳየት እንድንችል በሌሎች ሥራዎችም አብሮ መቆም የዘወትር ተግባር እንዲሆን አደራ ብለዋል፡፡

805 ነጥብ 3 ሚሊየን ችግኞች በመትከል የተያዘውን እቅድ ማሳካት እንደተቻለም በመግለጽ፤ በመርሃ ግብሩ ህጻናት፣ ሴቶች፣ ወጣቶች፣ አዛውንቶች፣ አካል ጉዳተኞች በሚያስደንቅ ብርታት ሃገራቸውን ለማልበስ ተስፋን ለመትከል ሙሉ ቀን ያሳዩት ተጋድሎ ለእኛ ከፍተኛ ሞራልና ተስፋ የሰጠ ነው ብለዋል፡፡

ለዚህም እንኳን ደስ አላችሁ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የዘንድሮውን የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ተስፋን መትከል አለብን ካልንበት ቀን አንስቶ እስከ ዛሬ 6 ነጥብ 5 ቢሊየን ገደማ ችግኝ ተተክሏልም ሲሉ ገልጸዋል፡፡

ቀሪው 1 ነጥብ 5 ቢሊየን ደግሞ በቀሪ ወራት እንደሚፈጸም በማንሳት በዛሬው የአንድ ጀምበር የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የበኩላቸውን ድርሻ ለተወጡ ሁሉ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review