አዲስ ሚዲያ ኔትወርክ በኢትዮጵያ ከሚገኙ ጠንካራ ሚዲያዎች አንዱ እንዲሆን የቀድሞ ቦርድ አባላት አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው -አቶ ሞገስ ባልቻ

AMN – ሐምሌ 30/2018 ዓ.ም

አዲስ ሚዲያ ኔትወርክ በአገሪቱ ከሚገኙ ጠንካራ ሚዲያዎች አንዱ ሆኖ እንዲቀጥልና የአዲስ አበባ አንደበት ሆኖ እንዲዘግብ አስተዋጽኦ ላበረከቱ የቀድሞ የቦርድ አባላት የእውቅና መርሃ ግብር ተካሂዷል።

በመርሃ ግብሩ የአዲስ ሚዲያ ኔትወርክ ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ሞገስ ባልቻን ጨምሮ የቀድሞ እና አዲስ የቦርድ አባላት እንዲሁም የተቋሙ አመራሮች ተገኝተዋል።

የቦርድ ሰብሳቢው አቶ ሞገስ ባልቻ ባስተላለፉት መልዕክት፤ ተቋሙ አሁን ለደረሰበት ደረጃ የበቃው የቀድሞ ቦርድ አባላት በአዳዲስ እይታዎች፣ በተለያየ እምቅ አቅም፣ ልምድ፣ በቁጭትና በትልቅ ውግንና በመመራታቸው ጭምር እንደሆነ ገልጸዋል።

አያይዘውም ዛሬ አዲስ ሚዲያ ኔትወርክ በኢትዮጵያ ውስጥ ከሚገኙ ጠንካራ ሚዲያዎች አንዱ ሆኖ የቀጠለው በቀድሞ አባላቱ ትልቅ ሌጋሲና አስተዋጽኦ ጭምር መሆኑን አንስተዋል።

በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የቀድሞ የቦርድ አባላትም በተቋሙ ቆይታቸው ያሳለፉትን አዎንታዊ ተሞክሮ አጋርተዋል።

ከባለሙያዎች ጋር የመገናኘትና የመተሳሰር እድል እንዳገኙ የገለጹት የቀድሞ የቦርድ አባል ዳኛቸው አሰፋ(ዶ/ር) ፣ ከተቋሙ ጋር ያላቸው ግንኙነት ሁልጊዜም እንደሚቀጥልና ለተቋሙ ሁልጊዜም በጎ እንደሚያስቡ ተናግረዋል።

ሌላው የቀድሞ የቦርድ አባል አቶ መሃመድ ካሳ በበኩላቸው አዲስ አበባ የአፍሪካ ድምጽ መሆን እንዳለባት በመጥቀስ፤ ሚዲያው ይህንን ተልዕኮ በብቃት እየተወጣ እንደሚገኝና ቦርዱ የነበረው ነጻነትና የሥራ ከባቢ በጣም የሚደነቅ መሆኑን አንስተዋል።

በቆይታቸው ብዙ መማራቸውን የጠቀሱት የቀድሞ የቦርድ አባሉ ብርሃኑ ሌንጂሶ(ዶ/ር)፣ አዲስ ሚዲያ ኔትወርክ ሰፊ ለውጥ ማሳየቱን አጽንኦት ሰጥተዋል።

በመጨረሻም አዲሶቹ የቦርድ አባላት የተጀመሩ ተስፋ ሰጪ ሥራዎችን ከዚህ በላይ አጠናክረው በመቀጠል የተቋሙን ራዕይ ከፍ ወዳለ ምዕራፍ እንደሚያደርሱት እምነት ተጥሎባቸው መርሃ ግብሩ ተጠናቋል።

በፍሬሕይወት ብርሃኑ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review