የምክክር ጉባኤው የተለያዩ ሀሳቦች በነፃነት እንዲንሸራሸሩና ልዩነቶችን በምክክር ለመፍታት ሰፊ ዕድል ፈጥሯል-ተመካካሪዎች

You are currently viewing የምክክር ጉባኤው የተለያዩ ሀሳቦች በነፃነት እንዲንሸራሸሩና ልዩነቶችን በምክክር ለመፍታት ሰፊ ዕድል ፈጥሯል-ተመካካሪዎች

AMN – ነሐሴ 7/2018 ዓ.ም

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ የተለያዩ ሐሳቦች በነፃነት እንዲንሸራሸሩ በማስቻል፣ ነባር ችግሮችን በምክክር ለመፍታት ሰፊ ዕድል መፍጠሩን ተመካካሪዎች ገለጸዋል።

በሀገር ውስጥና በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን የሚወክሉ አራት ሺህ ተመካካሪዎች ከሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ በስምንት ዐበይት አጀንዳዎች ላይ የጋራ መግባባት ለመፍጠር ጥልቅና አሳታፊ ምክክር እያካሄዱ ይገኛል።

አስተያየታቸውን የሰጡ ተመካካሪዎች በምክክሩ እየተነሱ የሚገኙት ሀሳቦች ለዘላቂ የሀገር ግንባታ አስተዋጽኦ የሚያበረክቱ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ከተመካካሪዎቹ መካከል የሲቪክ ማህበረሰብ ተቋምን በመወከል እየተመካከሩ የሚገኙት ተመካካሪ አብዲሳ አበበ(ዶ/ር) ፤ ምክክሩ ከመላው ኢትዮጵያ የተውጣጡ የህብረተሰብ ክፍሎች እየተሳተፉበትና ሁሉም ሰው ሀሳቡን በነፃነት እያቀረበበት ይገኛል ብለዋል።

ምክክሩ የተለያዩ ሀሳቦች ያለ ገደብ እንዲነሱ ዕድል መፍጠሩን ጠቁመው፤ ይህም በችግሮች ላይ አሳታፊ በሆነ መንገድ በመመካከር ለዛሬ ብቻ ሳይሆን ለነገ የሚበጁ መፍትሄዎችን ማምጣት እንደሚያስችል ተናግረዋል።

በተመካካሪዎች እየተነሱ ያሉት ሀሳቦች ኢትዮጵያን ወደ ዘላቂ ሰላም፣ ከፍታና እድገት ለማሻገር እንደሚያግዝ ገልፀው፤ ሂደቱ ለሀገሪቱ የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታም ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው ብለዋል።

የሲዳማ አርነት ንቅናቄ ፓርቲ ተወካይ ስማቸው እንግሶ በበኩላቸው፤በኢትዮጵያ ታሪክ በርካታ ሕዝብ በአንድ ላይ ሲመካከር የመጀመሪያው መሆኑን ገልጸው፤ በምክክሩ እየተነሱ ባሉ ሐሳቦች ላይ በመምከር ወደ አንድ የጋራ መግባቢያ እየተመጣ መሆኑን ጠቁመዋል።

ምክክሩ ለችግሮች ዘላቂ መፍትሄ ለማበጀት ትልቅ ዕድል መፍጠሩን ጠቁመው፤ ይህም የተሻለች ሀገርን ለመጪው ትውልድ ለማስረከብ እንደሚያግዝ ተናግረዋል።

ሀገራዊ ምክክሩ ኢትዮጵያ ሕብረ ብሔራዊነቷን በማጠናከር ከአፍሪካ አልፋ በዓለም አቀፍ ደረጃ አዎንታዊ ሚና እንድትጫወት የሚያስችል አስተዋጽኦ እንዳለው መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review