ከንቲባ አዳነች አቤቤ በትላንትናው ዕለት ለምክር ቤት አባላት ባደርጉት ንግግር በቀጣይ 5 ዓመታት ”ያጠፋነውን በማረምና ያጎደልነዉን በመሙላት ስህተታችንን ከህዝብ ሳንደብቅ የትናንቱ መልካም ስራችንን በላቀ ደረጃ እናስቀጥላላን” ሲሉ ተናግረዋል።
በተለይም የኑሮ ጫናን በተጨባጭ ማሻሻል በሚችሉ ስራዎች በተመለከተ የቅድሚያ ቅድሚያ ተሰጥቶ እንደሚሰራና በዚህም አመራሩ የተሰጠው ስልጣን መብት ሳይሆን አደራ መሆኑን ተገንዝቦ መስራት እንደሚገባው ነዉ ያነሱት፡፡
በሌላ በኩል ዜጋን በእኩል እና በክብር የሚያገለግል ተቋማትን መገንባት፣ ከሌብነትና ከብልሹ አሰራር የፀዳ አሰራር ማጠናከር ይህንንም የሚፀየፍ ማህበረሰብ መገንባት፣ፈጣን፣ዘመናዊ አገልግሎትን በማስፋትና ተደራሽ በማድረግ ዲጂታል ትራንስፎርማሽንን ማረጋገጥ እና የመዲናዋ የዲጂታል ኢትዮጵያን የ2030 ራዕይ ማሳካት ሌላኛው የትኩረት አቅጣጫ እንደሆነ ተናግረዋል።

በተለይም የስራ ዕድል እና ሃብት የበለጠ የሚፈጥር ኢኮኖሚን ማስፋትና መገንባት የዋጋ ንረትን መቆጣጠር እና የኑሮ ውድነትን መቀነስ፣ዘመናዊ የግብይት ስርዓትን ማስፋፋት፣ለወጣቶች ለሴቶች ሰፊ የስራ እድሎችን ማመቻቸት፣ኢንቨስትመንትን ማሳደግ፣የንግድ ስርዓትን ማዘመን፣አነስተኛና እና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎችን ማስፋፋት እና ጥቃቅን ኢንተርፕራይዞችን ማበረታታት እንዲሁም ቴክኖሎጂንና ፈጠራን በመደገፍ አዲስ አበባ ሃብት እና የስራ እድል የሚፈጠርባት ከተማ ለማድረግ 24/7 እንደሚሰራ ነዉ የተናገሩት ።
አዲስ አበባ ለኑሮ የምትመች፣የነዋሪዎቿን ክብር የምትጠብቅ ከተማ እንድትሆን ማስቻልና እንዲሁም ጥራት ያለዉ ሰፊ መሰረታዊ ልማቶችን መገንባት፣ያረጁና የጎሰቆሉ አካባቢዎችን ማደስና መልሶ መገንባት፣የንፁህ መጠጥ ዉሃ፣የመንገድ፣የፍሳሽ አወጋገድ፣የትራንስፖርት እና የመኖሪያ ቤት ተደራሽነት ማረጋገጥ እና ዘመናዊ ህክምና ማዕከላትን ማስፋፋት፣ የግሉን ዘርፍም ማበረታታትና የጤና ቱሪዝምን ማሳደግ እና የቀዳማይ ልጅነት ፕሮግራምን ማጠናከር ጨምሮ የትምህርት ፍትሃዊነት ማሻሻል ላይ በትኩረት እንደሚሰራ ነዉ ያስገነዘቡት ።
በመጨረሻም ”ያጠፋነውን በማረምና ያጎደልነዉን በመሙላት ስህተታችንን ከህዝብ ሳንደብቅ የትላንቱን መልካም ስራ በተሻለ እናስቀጥላላን” ሲሉ መልዕክታቸዉን አስተላልፈዋል።