AMN – ነሐሴ 8/2018 ዓ.ም

ሙስና እና ሌብነት የሀገርን ሁለንተናዊ እድገት ከማስተጓጎል ባለፈ የኢኮኖሚ እድገትን የሚገታ ነው፡፡
መንግሥት ሌብነትን ለማስወገድ እንዲሁም የሀገርና የሕዝብ ሀብት እንዲመለስ የወሰደው የህግ ማስከበር ሥራ ተስፋ ሰጪ ጅምር ነው።
የፀረ-ሙስና ተቋማት እንዲሁም የጸጥታ አካላት በጋራ በመቀናጀት ባከናወኗቸው ሥራዎች ሌብነት ላይ ጠንካራ ርምጃ ተወስዷል፡፡
ርምጃው ህግ የማክበር ባህልን ለማስረፅ እንዲሁም የተጭበረበረ ሀብትን ለመመለስ ወሳኝ ሚና ይኖረዋል።
ከዚህም ባለፈም ኢኮኖሚውን ከህገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውር ተጽእኖ ነፃ ለማድረግ እና ፍትሃዊ የገበያ ስርዓት እንዲዘረጋ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል፡፡
በህገ-ወጥ መንገድ የተገኘ ገንዘብ ላይ የተደረጉ ክትትሎችና የተወሰዱ ርምጃዎች የህግ የበላይነት እየሰፈነ ስለመምጣቱም ማሳያዎች ናቸው፡፡
ይህ ጅምር የተሳካ እንዲሆን ተቋማዊ አሰራርን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ማዘመን ወሳኝ ነው። የሙስና ቀዳዳዎችን በዲጂታል አሰራር መዝጋት እንዲሁም የአገልግሎት አሰጣጡን ግልጽ ማድረግ የርምጃውን ውጤታማነት ከፍ ያደርገዋል።
በሌላ በኩል የሚወሰደው ርምጃ ለህዝብ ግልጽ በሆነ መንገድ መቅረቡ ለአስተማሪነቱ ፋይዳው ጉልህ ነው።
ህዝቡም በየደረጃው የሚፈጸመውን ሌብነት እና ሙስናን በንቃት በመከታተል መረጃ መስጠት ይጠበቅበታል፡፡ ይሄም የፀረ ሙስና ትግሉን አድማስ ያሰፋዋል።
መንግሥት የጀመረው ህግ የማስከበር ርምጃ ፍትህን ከማስፈን ባለፈ መልካም አስተዳደርን እውን ለማድረግ ወሳኝ ምዕራፍ ነው።
በወርቅነህ አቢዮ