AMN – ነሐሴ 8/2018 ዓ.ም

የመደመር መንግሥት የፈጠራቸውን መልካም እድሎች በመጠቀም ለሀገር ልማት በጋራ መትጋትና ብልሹ አሰራሮችንም መዋጋት ይገባል ሲሉ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ እውነቴ አለነ ገለጹ።
የፌዴራል ስነ-ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን 25ኛ ዓመት የብር ኢዮቤልዩ በዓል ማጠቃለያ መድረክ “የፀረ ሙስና ትግል ትናንት ዛሬ እና ነገ በሚል መሪ ሀሳብ” በአዳማ እየተካሄደ ይገኛል።

በመድረኩ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ እውነቴ አለነ፤ የሙስና ትግል የመጀመሪያ ምዕራፍ መከላከልን፣ ምርመራንና ክስን በአንድ ተቋም በማድረግ ይሰራ እንደነበር አስታውሰዋል።
ሆኖም እንቅስቃሴው ህዝብን የትግሉ ባለቤት ያላደረገ፣ የሙስና መከላከል ስራን የረሳና ለትውልድ የስነ-ምግባር ግንባታ ቦታ የማይሰጥ ነበር ብለዋል።

በሁለተኛው ምዕራፍ፣ ከሚሊኒየሙ መባቻ ጀምሮ ለውጡ እስከመጣበት ጊዜ ድረስ የነበረው ወቅት በልማታዊ መንግሥት ስም ከፍተኛ ጣልቃገብነት የተካሄደበት እንዲሁም ሙስና በከፍተኛ ሁኔታ የተስፋፋበት እንደነበር አንስተዋል።
በዚህም ምክንያት የህዳሴ ግድብን ጨምሮ የተለያዩ ሜጋ የመንግሥት ፕሮጀክቶች በሙስና እና በሌብነት ምክንያት ለከፍተኛ ችግር ተዳርገው እንደነበር ተናግረዋል።

በሶስተኛው ምዕራፍ፣ ማለትም ከሀገራዊ ለውጡ መባቻ ጀምሮ እስካሁን ባለው ጊዜ ውስጥ ከሙስና ትግል አኳያ መሰረታዊ ለውጥ መደረጉን ገልጸዋል።
በኮሚሽኑ ላይ ከተደረጉት ማሻሻያዎች መካከል ዋነኛው የህግ ሪፎርም መሆኑን አንስተው፤ ሙስናን በአንድ ተቋም ብቻ መታገል ስለማይቻል ሁሉም የመንግሥት ተቋማት የትግሉ ባለቤት እንዲሆኑ መደረጉን አብራርተዋል።
በሶስቱም የመንግሥት አካላት መካከል ጥብቅ የመረጃ ቅብብሎሽ፣ ጠንካራ ትስስር እና ቅንጅት እንዲፈጠር የሚያስችል ለውጥ ተደርጓልም ነው ያሉት።

ይህም ስርዓታዊ እና መንግሥታዊ ሙስና መሰረት እንዳይኖረውና እንዳይፈጠር ለማድረግ የሚያስችል የሚያበረታታ ፖለቲካዊ ቁርጠኝነት የታየበት መሆኑን ገልጸዋል።
በተለይም የዲጂታላይዜሽንን መልካም እድሎች በመጠቀም አገልግሎቶችን ከሰው ንክኪ ነፃ እና አካታች በሆነ መንገድ ማቅረብ መቻሉ፣ መሰረታዊ የእሳቤ ለውጥ ማምጣቱንና ለፀረ-ሙስና ትግሉ ጠንካራ መሰረት እየጣለ እንደሚገኝ አክለው ጠቁመዋል።
በእነዚህ አዎንታዊ ለውጦች እና የመደመር እሳቤ በፈጠራቸው አዳዲስ እድሎች በመጠቀም፣ በአሁኑ ወቅት ሙስና ጎልቶ በሚታይባቸው ዘርፎች ላይ ያተኮረ ዘመቻ መጀመሩን ለአብነት አንስተዋል።
በመሆኑም የተጀመሩ አዎንታዊ ስራዎችን አጠናክሮ በመቀጠል፣ በመጪው ጊዜም ያልተቋረጠና የተቀናጀ የሙስና ትግል ማድረግ እንደሚገባ አሳስበዋል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው፡፡
የፌዴራል ስነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ እሸቴ አስፋው በበኩላቸው፣ ባለፉት ዓመታት ኮሚሽኑ ሙስናንና ብልሹ አሰራርን ለመታገል የሚያስችሉ ስትራቴጂዎችን ነድፎ ሲንቀሳቀስ መቆየቱንና በዚህም አበረታች ውጤቶች መመዝገባቸውን ገልጸዋል።
25ኛ ዓመታችንን ስናከብርም ጠንካራና ደካማ ጎኖቻችንን ነቅሰን በማውጣት በቀጣይ የተሻለ ሥራ ለመሥራት ዝግጁነታችንን እያረጋገጥን ነውም ብለዋል።
ኮሚሽኑ የሙስና እና የብልሹ አሰራር ችግሮችን በመፍታት፣ ተጠያቂነትን በማስፈንና የህዝብን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የጀመራቸውን ተግባራት ለማሳለጥ በሚያስችል ጠንካራ ቁመና ላይ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።
በተለይም ከሀብት ምዝገባ አንጻር አዎንታዊ ለውጦች መኖራቸውን ያነሱት ምክትል ኮሚሽነሩ፣ ሀብታቸውን ባላስመዘገቡ አካላት ላይ ተጠያቂነትን የማስፈን ሥራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
በመድረኩ ላይ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈ-ጉባኤ ወይዘሮ ሎሚ በዶን ጨምሮ ከፌዴራልና ከሁሉም ክልሎች የተወጣጡ ከፍተኛ አመራሮችና ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።