AMN – ነሐሴ 11/2018 ዓ.ም
ኢትዮጵያ ባለፉት የለውጥ ዓመታት በውጭ ግንኙነትና በዲፕሎማሲ መስክ ተግባራዊ ያደረገችው ስልታዊ ለውጥ፣ ሀገሪቱን በዓለም አቀፍ መድረክ ተጽዕኖ ፈጣሪ ከማድረጉም በላይ ብሔራዊ ጥቅሟን በማስከበር ረገድ ትልቅ ፋይዳ አስገኝቷል።
ሀገሪቱ ባለፉት ዓመታት ውስጥ በርካታ ውስጣዊ ፈተናዎችንና ዓለም አቀፍ ጫናዎችን ተቋቁማ በዲፕሎማሲው መስክ ባሳየችው ቁርጠኝነትና ስልታዊ አቀራረብ በቀጠናውና በዓለም አቀፍ መድረክ ያላትን ተሰሚነት ከፍ ማድረግ ችላለች።
ኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት መርሆቿን በጋራ ተጠቃሚነትና ሉዓላዊነትን በማክበር ላይ የመሠረተች ሲሆን፤ በዚህ ማዕቀፍ ውስጥ የተመዘገቡት ድሎች ሀገሪቱን ከፍ ያለ ደረጃ አድርሰዋታል።
በተለይም የብሪክስ አባል መሆኗ ለደቡብ-ደቡብ ትብብር አዲስ በር የከፈተ ሲሆን፤ አባልነቱ ለኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ አማራጮችን በማስፋት እና በዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ተቋማት ውስጥ የነበራትን ድምፅ ከፍ ለማድረግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል።
ከዚህም በተጨማሪ በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ዙሪያ የተደረገው የዲፕሎማሲ ትግል ሀገሪቱ የተፈጥሮ ሀብቷን ፍትሃዊ በሆነ መንገድ የመጠቀም መብቷን ለማስከበር ያስቻለ ድል የተገኘበት ነው፡፡

በአፍሪካ ቀንድ ሰላም እንዲሰፍን በኢጋድ እና በአፍሪካ ሕብረት በኩል የምታደርገው ቀጣይነት ያለው ጥረት ለጎረቤት ሀገራት መረጋጋት የላቀ አስተዋጽኦ አበረክቷል።
ይህ የዲፕሎማሲ ስኬት ለሀገሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገትም ጠንካራ መሠረት አኑሯል።
ከተለያዩ ሀገራት ጋር የተፈጠሩ አዳዲስ የትብብር ስምምነቶች የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ፍሰት እንዲጨምርና የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲፋጠን አድርገዋል።
በተለይም የተደረጉ የሁለትዮሽ ግንኙነቶች የንግድና የቱሪዝም ዘርፎችን በማነቃቃት ረገድ አመርቂ ውጤቶችን አስመዝግበዋል።
በተጨማሪም በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በዲፕሎማሲው ሂደት ውስጥ ያላቸውን ተሳትፎ ማጠናከራቸው ለሀገር ገጽታ ግንባታና ለልማት ሥራዎች ትልቅ አቅም ፈጥሯል፡፡
የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ፤ ሀገሪቱ በዓለም አቀፍ መድረክ ያላትን ተሰሚነት ይበልጥ ለማጠናከር እና በአፍሪካ ደረጃ የፍትሃዊ ውክልና ተሟጋችነቷን አጠናክሮ ለማስቀጠል ቁልፍ ሚና ይጫወታል።
በበረከት ጌታቸው