AMN- ነሐሴ 12/2018 ዓ.ም

ኢትዮጵያ የዓረቢካ ቡና መገኛና የተፈጥሮ ሀብት ባለቤት ናት።
ከአረንጓዴው የደቡብ እና ደቡብ ምዕራብ የሀገሪቱ ክፍሎች የሚመነጨው የጫካ ቡና፣ ጣዕሙና መዓዛው ብቻ ሳይሆን ታሪካዊና ሥነ-ምህዳራዊ እሴቱ ተጠብቆ ለትውልድ የተሸጋገረ ድንቅ የባህል እሴትም አለው።
ለኢትዮጵያውያን ቡና ከዕለታዊ መጠጥነቱ ባለፈ ከ15 ሚሊየን በላይ ዜጎች የኑሮ መሠረትና የሀገሪቱ የውጭ ምንዛሬ ዋነኛ ምንጭም ነው።
ከአነስተኛ አምራቾች እስከ ላኪዎችና የቡና ተረካቢዎች ድረስ ሚሊየኖችን በስራ እድልና ገቢ ያስተሳስራል ያናብባል።
በኢትዮጵያውያን ዘንድ ቡና አብሮ መጠጣት ማህበራዊ መቀራረብን፣ አብሮነትን፣ መደጋገፍን ችግሮችን መፍታትን እና እውቀትና ልምድን የመጋራት ዕድልን ይፈጥራል፡፡

የቡና ሥነ-ስርዓት የእርቅ፣ የምክር፣ የደስታና የሀዘን መጋሪያ የእንግዳ ተቀባይነት እና መከባበር መገለጫ የሆነ የሕይወት መድረክ ነው።
ኢትዮጵያ በተለያዩ የቅርስ ሀብቶች የታደለች ከመሆኗ ባሻገር በርካታ የቱሪስት መሰህቦችን በዓለም ደረጃ ለማስመዝገብ የቻለች ሀገር ናት።
በዩኔስኮ በዓለም ቅርስነት ከተመዘገቡ ቅርሶች መካከልም የአክሱም ሐውልት፣ የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት፣ የመስቀል በዓል፣ የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ፣ የጎንደር ቤተ-መንግስት፣ የጢያ ትክል ድንጋዮች፣ የታችኛው አዋሽ ሸለቆ፣ የሐረር ጁገል ግንብ፣ የገዳ ሥርዓት እና ፍቼ ጫምባላላ ሊጠቀሱ ይችላሉ፡፡

ድንቅ የተፈጥሮ ስጦታና ከትውልድ ትውልድ ሲሸጋገር የመጣው ባህላዊ የቡና አፈላል ሥነ-ሥርዓትም፣ በዩኔስኮ የማይዳሰስ ባህላዊ ቅርስነት ለማስመዝገብና ለሀገር ውስጥም ሆነ ዓለም አቀፍ ዕውቅና ለማብቃት የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን፣ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት የመረጃ ማሰባሰብ እና የዝግጅት ሥራዎችን እየሰራ እንደሚገኝም ተመላክቷል።

ይህም ኢትዮጵያ ለዓለም ካበረከተቻቸው ገጸ-በረከቶች መካከል ቡና ቀዳሚው መሆኑን ዳግም የሚያረጋግጥ ኩራት ይሆናል።
በኢትዮጵያ የጫካ ቡናዎች በተፈጥሮ ደን ጥላ ስር የሚበቅሉ በመሆናቸው፣ ደኑ ሳይደፈርና ሳይቆረጥ እንዲቆይ ትልቅ አስተዋፅዖ አላቸው።
የቡና ተክል ጥበቃ የደን ጥበቃ ነው፤ የደን ጥበቃ ደግሞ የዓለም አየር ንብረት ሚዛን መጠበቂያ ነው።
በመሆኑም እያንዳንዱ የኢትዮጵያ ቡና ሲፈላ፣ ታሪክ፣ ባህል፣ የተፈጥሮ ጥበቃና የሰው ልጅ ወዳጅነት በአንድ ሲኒ ይቀርባል።
በታምራት ቢሻው