AMN- ሰኔ 25/2018 ዓ.ም

በአንጻራዊ ሰላምና መረጋጋት ውስጥ ላሉ ሀገራት በአንድነት መቆም የጋራ ጥቅም ቢሆንም፣ በውስጣዊ ግጭትና በፖለቲካ መዘበራረቅ ለክፉ ቀኖች የተዳረጉ ሀገራት ግን በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ማለፍ ግድ ይላቸዋል።
ታድያ እነዚህ ሀገራት ከመፈራረስ አደጋ ለመዳን የተጠቀሙበት ዋናው መሳሪያ “ሀገራዊ ምክክር” ሲሆን፣ ይህ ሂደት የሕዝቦችን የጋራ መግባባት በመገንባት እንደ አዲስ ለመጀመር አስችሏቸዋል።
ለማሳያም የአፍሪካዊቷ ቱኒዚያ ለዚህ ምርጥ ተሞክሮ ትጠቀሳለች።
እ.አ.አ በ2013 ሀገሪቱ ወደ ትርምስ በምትገፋበት ወቅት፣ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች የመሩት “ሀገራዊ የውይይት ስብስብ” ጣልቃ በመግባት የተፈጠረውን የፖለቲካ ቀውስ በውይይት መፍታት ችለዋል።
ይህ እርምጃ ሀገሪቱን ከእርስ በርስ ጦርነት መታደግ ብቻ ሳይሆን፣ ለሰላም የኖቤል ሽልማት እንዲበቁ አድርጓቸዋል።
ሌላኛው ተጠቃሽ ሀገር ደቡብ አፍሪካ ናት፣ የአፓርታይድ ስርዓት ካከተመ በኋላ ሀገሪቱ ወደ ጥቁርና ነጭ ጦርነት ትገባለች ተብሎ ሲጠበቅ፣ የኔልሰን ማንዴላ እና የሌሎች መሪዎች የውይይት ጥረት የ”እውነትና እርቅ ኮሚሽን” እንዲቋቋም አስቻለ።
ይህ የውይይት መድረክ ያለፈውን በደል በመነጋገርና ይቅር በመባባል አዲሲቷን ዲሞክራሲያዊት ደቡብ አፍሪካን ለመገንባት መሠረት ጥሏል።
በአውሮፓ በኩል የሰሜን አየርላንድ ጉዳይ የሚነሳ ሲሆን፣ ለዓመታት የዘለቀው ደም አፋሳሽ ግጭት በ1998 በተፈረመው “የዓርብ ዕለት ስምምነት” (Good Friday Agreement) ሊቆም ችሏል።
የሁሉም ወገኖች ተሳትፎ የተረጋገጠበት ይህ ሰፊ የፖለቲካ ውይይት፣ ጠመንጃን በመተው በዴሞክራሲያዊ መንገድ የፖለቲካ ግቦችን ማሳካት እንደሚቻል ዓለም አቀፍ ትምህርት ሰጥቷል።
የኮሎምቢያ መንግስት ከአማፂያን ጋር ያደረገው ረጅም የሰላም ውይይትም ሌላው ጉልህ ተሞክሮ ነው።
ለአምስት አስርት ዓመታት የዘለቀው ግጭት በውይይት መፈታቱ፣ ሁለቱም ወገኖች የፖለቲካ ልዩነታቸውን በድርድር እንዲፈቱና ሰላማዊ የመንግስት አስተዳደር እንዲያሰፍኑ አስችሏቸዋል።
ይህ ሂደት ሀገራዊ ምክክር የረጅም ጊዜ ትዕግስትና ቁርጠኝነትን የሚጠይቅ መሆኑን ያሳያል።
የእነዚህ ሀገራት የጋራ መገለጫ፣ ምክክርን እንደ ድክመት ሳይሆን እንደ ጥንካሬ መውሰዳቸው ነው።
ችግሮችን በውይይት መፍታት የዜጎችን ደህንነት የሚያረጋግጥ፣ የማኅበራዊ መስተጋብርን የሚያጠናክርና ለኢኮኖሚ እድገት የላቀ በር የሚከፍት ነው።
የጋራ መግባባት ሲፈጠር፣ ሀገራት የውስጥ አቅማቸውን በማቀናጀት ከውጫዊ ተፅዕኖዎችም የመላቀቅ ዕድል ይኖራቸዋል።
ይሁን እንጂ በተቃራኒው፣ ምክክርን ችላ ያሉ ሀገራት መፈራረሳቸው የማይቀር መሆኑን ታሪክ ያስተምራል።
የፖለቲካ ምህዳሩ ሲጠብ፣ የልዩነት ድምፆች ሲታፈኑ እና የጋራ መግባባት ሲጠፋ፣ ሀገራት በቀላሉ ወደ ደካማ መንግስትነት ይወርዳሉ።
በመሆኑም ሀገራዊ ምክክር የሰላም አማራጭ ሳይሆን የህልውና ዋስትና መሆኑ አይቀሬ ነው።
ኢትዮጵያም ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽንን በማቋቋም ሀገራዊ ስብራቶችን በምክክር ለመፍታት የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ ትገኛለች።
ታዲያ ሀገራዊ ምክክር በአንድ ጀምበር የሚፈታ ሳይሆን የሂደት ውጤት ጭምር ሲሆን፣ የሁሉንም ወገን ተሳትፎ፣ እውነተኛ ፍላጎትና ለጋራ ጥቅም ሲባል የሚደረግ ስምምነትን ይፈልጋል።
በዓለም ላይ ስኬታማ የሆኑ ሀገራት ያሳዩን እውነት፣ ሰላም የውይይት ውጤት እንጂ የግዳጅ ውጤት አለመሆኑንም ጭምር ነው።
በሚካኤል ህሩይ