AMN- ነሐሴ 13/2018 ዓ.ም
ኢትዮጵያዊያን በርካታ ግድቦችን የመገንባት አቅሙም ዝግጁነቱም እንዳላቸው የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ፕሮጀክት ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አረጋዊ በርሄ (ዶ/ር) ተናገሩ።
የጽሕፈት ቤቱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አረጋዊ በርሄ (ዶ/ር)፤ ታላቁ የሕዳሴ ግድብ የዓባይ ውሃ ፍትሃዊ አጠቃቀም ላይ ለዘመናት የቆየ የተዛባ አረዳድን የቀየረ መሆኑን ተናግረዋል።
ግድቡ የትኛውንም ሀገር እንደማይጎዳና ይልቁንም ቀጣናውን በኢነርጂ እያስተሳሰረ መሆኑ በተግባር መረጋገጡን ጠቅሰዋል።
ነገር ግን ግብጽ ይህንን እውነታ በመካድ አሁን ላይ የቀደመ በጩኸት የማደናገር ተግባሯን በስፋት እያከናወነች መሆኑን ተናግረዋል።
ዓባይ የተፋሰሱ ሀገራት በትብብር የሚጠቀሙት ሃብት እንጂ የግብጽ የግል ንብረት አይደለም ያሉት አረጋዊ (ዶ/ር)፤ከዚህ አኳያ የግብጽ የማደናገር ዘመቻ ሊቆም ይገባል ነው ያሉት። ኢትዮጵያ ዋነኛ ዓላማ በትብብር ማደግ መሆኑንም አብራርተዋል።
ኢትዮጵያዊያን በትብብር ምን ማሳካት እንደሚችሉ በታላቁ የሕዳሴ ግድብ ግንባታ ማሳየታቸውን አንስተው፤ በቀጣይም በርካታ ግድብ የመገንባት አቅሙም ዝግጁነቱም አላቸው ብለዋል።
በታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ወቅት ሕዝብን በማስተባበር ረገድ በርካታ ጠቃሚ ልምድ መገኘቱንም ተናግረዋል።
ይህ ልምድ በቀጣይ ለሚከናወኑ መሰል የልማት ስራዎች ትልቅ ግብዓት መሆኑን መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።