AMN- ነሐሴ 14/2018 ዓ.ም
ኢትዮጵያና ሩሲያ በቴክኖሎጂ ዘርፍ ያላቸውን ትብብር ይበልጥ ለማጠናከር በትኩረት እየተሰራ ነው ሲሉ በኢትዮጵያ የሩሲያ አምባሳደር ኤቭጌኒ ቴርኪን ገለጹ፡፡
በኢትዮጵያ የሩስያ አምባሳደር ኤቭጌኒ ቴርኪን የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩትን ጎብኝተዋል።
የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ወርቁ ጋቸና (ዶ/ር)፤ ኢንስቲትዩቱ በሀገሪቱ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ጉዞ ውስጥ እያከናወናቸው ያሉ ወሳኝ ስራዎችን አስመልክተው ለአምባሳደሩ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ዋና ዳይሬክተሩ ኢንስቲትዩቱ የሚያከናውናቸው የምርምርና ልማት ስራዎች በኢትዮጵያ ቅድሚያ በተሰጣቸው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች ላይ ከፍተኛ እምርታ እንዲመዘገብ ማስቻላቸውን ተናግረዋል፡፡
አምባሳደር ኤቭጌኒ ቴርኪን በበኩላቸው፤ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ጠንካራ ትብብር እና የረጅም ጊዜ የሁለትዮሽ ግንኙነት በማንሳት በምርምርና ልማት፣ በሰው ሃይል ልማት እና ቴክኖሎጂ ሽግግር ላይ ኢትዮጵያ እና ሩስያ በጋራ እንደሚሰሩ ገልጸዋል።
ይህ የሁለቱ ሀገራት አጋርነት የብሪክስ አባል ሀገራት አርቲፊሻል ኢንተለጀንስን ለጋራ ዕድገትና ተጠቃሚነት ለማዋል ከሚያደርጉት ሰፊ ጥረት ጋር የሚጣጣም መሆኑን የኢንስቲትዩቱ መረጃ ያመላክታል፡፡