የመውሊድ በዓል ሲከበር የአብሮነትና የመደጋገፍ እሴቶችን በተግባር በማሳየት ሊሆን ይገባል

AMN -ነሐሴ 17/2018 ዓ.ም

የ1 ሺህ 501ኛው የነብዩ መሀመድ ልደት /መውሊድ/ ማክበርን ምክንያት በማደረግ በነብዩ ሙሀመድ ውልደት ላይ ያተኮረ የፓናል ውይይት ተካሂዳል፡፡

በውይይቱ ላይ ንግግር ያደረጉት የታላቁ አንዋር መስጂድ ምክትል ኢማምና የብሔራዊ መውሊድ አስተባባሪ ኮሚቴ አባል ሸይኽ አብዱልሐሚድ አህመድ የመውሊድ በዓል ከታላቁ ነብይ መልካም ስብዕናን፣ ቸርነትን፣ ደግነትን፣ ለሰው አሳቢነትን፣ ርህራሄና ሌሎችንም መልካም ስራዎቻቸውን የምናስታውስበት ነው ብለዋል፡፡

የመውሊድን በዓል ስናከብር የታላቁን ነብይ መልካም ስብእና ፍቅርና እዝነት በመሰነቅ የአብሮነትና የመደጋገፍ እሴቶችን በማስቀጠል መሆን አለበት ያሉት የመውሊድ አስተባባሪ ኮሚቴ አባል ሸይኽ አብዱልሐሚድ አህመድ የእሳቸውን መልካምነት በመላበስ የተቸገሩትን በመርዳት፣ በማገዝ፣ ሰላም ፍቅርና እዝነትን በተግባር በማሳየት መሆን እንዳለበት አስገንዝበዋል።

ኤ ኤም ኤን ያነጋገራቸው የሀይማኖት አባቶች የነብዩ መሀመድ መውሊድ በእስልምና ትልቅ ስፍራ ያለው መሆኑን በማንሳት የእርሳቸው ወደ እዚች ምድር መምጣት የብዙ ነገሮች መሰረትና የስኬት መንገድ የገለጠ ስለመሆኑ ጠቅሰው ከእርሳቸው ፍፁም ደግነት ፍቅርና እዝነት የተማርንበት ነው ብለዋል።

የፓናል ውይይቱን የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ከታላቁ አንዋር መስጂድ ወጣት ጀምዓ ጋር በመተባበር ያዘጋጁት ነው።

በመሃመድኑር አሊ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review