የ76ኛው የዓለም ጤና ድርጅት የአፍሪካ ቀጣናዊ ኮሚቴ ስብሰባ ተሳታፊዎች የእግር ጉዞ እያደረጉ ነው

AMN- ነሐሴ 17/2018 ዓ.ም

የ76ኛው የዓለም ጤና ድርጅት የአፍሪካ ቀጣናዊ ኮሚቴ ስብሰባ ተሳታፊዎች ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ለመከላከልና ጤናማ የአኗኗር ዘይቤን ለማስፋፋት ዓላማ ያደረገ የእግር ጉዞ እያካሄዱ ነው።

የእግር ጉዞው ከአድዋ ድል መታሰቢያ ተነስቶ በከተማዋ የእግረኛ መንገድ በመከተል መስቀል አደባባይ ላይ የሚጠናቀቅ ሲሆን “ንግግርን ወደ ተግባር” (Walk the Talk) በሚል መሪ ሐሳብ እየተካሄደ ነው።

በእግር ጉዞው የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባን ጨምሮ የአፍሪካ ሀገራት የጤና ሚኒስትሮች፣ ከፍተኛ የመንግሥት ሥራ ኃላፊዎች፣ የዓለም ጤና ድርጅት አመራሮች፣ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ኮማንደር ስለሺ ስህን እንዲሁም ሌሎች ታዋቂ አትሌቶች ተሳትፈዋል።

የጤና አመራሮቹ በጉዞው በመሳተፍ የአካል እንቅስቃሴ እንደ ስኳር በሽታ፣ የደም ግፊትና የልብ ሕመም ያሉ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን መከላከል ያለውን ጠቀሜታ በተግባር ለማሳየት ነው።

የእግር ጉዞው የጤና ፖሊሲ ውሳኔዎችን ወደ ተጨባጭ ተግባር ለመቀየርና በአፍሪካ ሕዝቦች መካከል ጤናማ የአኗኗር ዘይቤን ለማስፋፋት ያለመ ግንዛቤ ለመፍጠር መሆኑን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

የዓለም ጤና ድርጅት የአፍሪካ ቀጣናዊ ኮሚቴ 76ኛ ስብሰባ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ሲሆን በአፍሪካ የጤና ስልቶችና የቀጣይ አቅጣጫዎች ላይ ውይይት ያደርጋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review