AMN-ነሐሴ 25/2018 ዓ.ም

በጉበት ሴሎች ውስጥ ከመጠን በላይ ስብ የሚከማችበት የጉበት ስብ በሽታ በአሁኑ ወቅት በዓለም አቀፍ ደረጃም ሆነ በሀገራችን በከፍተኛ ሁኔታ እየተስፋፋ ያለ አሳሳቢ የጤና ችግር ሆኗል።
በሽታው በመጀመሪያዎቹ ደረጃዎች ላይ ምንም ዓይነት ግልጽ ምልክት የማያሳይ በመሆኑ “ዝምተኛው ገዳይ” የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል።
ጤናማ ጉበት አነስተኛ መጠን ያለው ስብ ሊኖረው ቢገባም፣ የስቡ መጠን ከጉበት አጠቃላይ ክብደት ከ 5 እስከ 10 በመቶ ሲበልጥ እንደ በሽታ ይታያል።

ጥናቶች እንደሚያመለክቱት ይህ ህመም አራት አደገኛ ደረጃዎች ያሉት ሲሆን፤ መጀመሪያ በቀላል የስብ ክምችት የሚጀምር ሲሆን ካልታከመ ግን ወደ ጉበት መቆጣት ከዚያም ወደ ጉበት ጠባሳ እና በመጨረሻም ወደማይመለስ የጉበት ካንሰር ወይም ሲሮሲስ ይሸጋገራል።
ለዚህ አደገኛ በሽታ ከሚያጋልጡ ዋና ዋና ምክንያቶች መካከል የሆድ አካባቢ ውፍረት (ቦርጭ) እና ከመጠን ያለፈ ውፍረት፣ የሁለተኛ ዓይነት ስኳር በሽታ፣ ከፍተኛ የደም ግፊት እንዲሁም ስኳር፣ ጣፋጭ መጠጦች፣ ከተፈተገ እህል ዱቄት የተዘጋጁ እና ቅባት የበዛባቸው ምግቦችን ማዘውተር ይጠቀሳሉ።
አብዛኞቹ ታካሚዎች ህመሙ መኖሩን የሚያውቁት ለሌላ ህመም አልትራሳውንድ ምርመራ በሚያደርጉበት ወቅት መሆኑን በየካቲት 12 ሕክምና ኮሌጅ የውስጥ ደዌ ስፔሻሊስት ሐኪም ዶ/ር ሰላም ቦጋለ ከኢ.ኤም.ኤን ጋር በነበራቸው ቆይታ ገልጸዋል።
ህመሙ ሥር ከሰደደ በኋላ በህክምናው ዘርፍ የሚያድን የተለየ መድኃኒት ስለሌለ፣ ዋነኛው መፍትሔው የአኗኗር ዘይቤን ማስተካከል መሆኑን ዶ/ር ሰላም አብራርተዋል።
በዚህም መሰረት ከሰውነት ክብደት ላይ ከ 5 እስከ 10 በመቶ መቀነስ እና ቦርጭን መቆጣጠር የጉበትን ስብ መጠን በከፍተኛ ሁኔታ ይቀንሳል።
በተጨማሪም አትክልት፣ ፍራፍሬ እና ፋይበር የበዛባቸው ምግቦችን ማዘውተር፤ ስኳር፣ ቅባት እና ነጭ የዱቄት ውጤቶችን መቀነስ እንዲሁም በሳምንት 5 ቀናት ለ30 ደቂቃ ፈጣን እግር ጉዞ ማድረግ በሽታውን ቀድሞ ለመከላከል ይረዳል።
አልኮልን ሙሉ በሙሉ ማቆምም ጉበት ራሱን እንዲያድስ ዕድል ይሰጣል።
የደም ውስጥ የስኳር እና የኮሌስትሮል መጠንን በተገቢው ሁኔታ መከታተልና መቆጣጠር ህመሙን ለመከላከል እና ለማከም አስተማማኝ መፍትሄ ነው።
በመሆኑ ማንኛውም ሰው ጤናማ የአኗኗር ዘይቤን በመከተል ራሱን ከዚህ አደገኛ በሽታ እንዲጠብቅ ዶ/ር ሰለሞን አሳስበዋል።
በበረከት ጌታቸው